“ክንዱን የቀመሱት ዳግም አይነኩትም፤ ያሰቡትም አይደፍሩትም”

10
ግርማ ሞገሱ እንደ አንበሳ ነው፤ በሩቅ ሲያዩት ያስበረግጋል፤ ሲቀርቡት ያሸብራል፤ ሲነኩት ደግሞ ክንዱ እንደ እሳት ይፋጃል፤ እንደ ንብ ይናደፋል፤ እንደ በርበሬ ይለበልባል፤ እንደ ኮሶ ይኮመጥጣል።
ክንዱን የቀመሱት ዳግም አይነኩትም፤ ያሰቡትም አይደፍሩትም፣ ከሞከሩም አይችሉትም፤ የሽንፈት ጽዋን ከመቀበል ውጭ አማራጭ የላቸውም።
ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ሥጋውን ቆርሶ ለዘመናት ሀገርን አጽንቷል።
እርሱን የነኩ ሁሉ የሽንፈት ካባ ተጎናጽፈው ጥቁር ታሪክ ጽፈዋል፤ ዳግም ላይነኩትም ምለው ተገዝተዋል። ብርታቱ ከብረት፣ ጽናቱ ከአለት ይጠነክራል፤ ድል ቁርሱ፣ ጀግንነት መለያው፣ አይበገሬነት ደግሞ መገለጫው ነው። ድል አድራጊነቱ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም የነገሠ ነው።
በታሪክ ማዕበል ውስጥ አልፋ በልጆቿ የጽናት ትክሻ ላይ ቆማ የምትጓዘውን የኢትዮጵያ ታላቅነት ስናስብ ከፊት ደምቆ የሚታየው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የማይደበዝዝ ደማቅ ገጽታ ነው።
እርሱ የሀገር ጠባቂ ብቻ አይደለም፤ የሀገር ፍቅር እሳት በልቡ የሚንቦገቦግ፣ የሕዝብ እንባ የሚጠርግ፣ የጽናት እና የጀግንነት ጥግ ነው።
የጥፋት ኀይሎችን ህዋስ ለይቶ በመምታት የተመሰከረለት ነው፤ በሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም እና ክብር አይደራደርም። በገነባው ወታደራዊ ቁመና የጠላቶቹ የበቀል ህልም ይመክናል፤ የጥፋት ሴራቸው ይከሽፋል፤ የጥላቻ ግንባቸውም ይፈርሳል።
ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ለቀጣናው ደኅንነት፣ ሰላም እና ጸጥታ ትልቅ መከታ እና አለኝታ ኾኖ ዘልቋል።
ይህ ሠራዊት በስሜት ሳይኾን በላቀ ወታደራዊ ሳይንስ እና የውጊያ ቀመር የሚመራ ነው። የጠላትን የጥፋት መንገድ አስቀድሞ የመተንበይ፣ ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የሚገጥሟትን ተደራራቢ ፈተናዎች በበሰለ ጥበብ እና በካበተ ልምድ የመመከት ሙሉ አቅም አለው።
ለራሱ ሕይወት ሳይሰስት «ቅድሚያ ለሀገሬ እና ሕዝቤ!» በማለት በከፈለው ውድ መስዋዕትነት የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ ነፃነት እና ኩራት ሳያስደፍር አስከብሮ አቁሟታል።
የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት እንደገለጹት «መከላከያ ሠራዊት ሰላም እንዳይደፈርስ የሚጠብቅ፣ የጠፋን ሰላም ለማምጣት የሚተጋ፣ የመጣ ሰላምን ለማጽናት የሚሠራ፤ ዋና ዓላማውም ሰላምን ማስፋት እና የሀገር ብልጽግናን ባልተቋረጠ መንገድ እውን ማድረግ ነው»።
ይህ ሠራዊት ግቡ በሚከፍለው የላብ እና የደም ዋጋ የሕዝብ እና የሀገርን ሉዓላዊነት ማስቀጠል ነው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ማዕከል የካቲት 1993 ያሳተመው አማርኛ መዝገበ ቃላት «ሠራዊት» ማለት ለአንድ ዓላማ በአንድ ቡድን ውስጥ የተሠባሠበ ሕዝብ ማለት ነው በማለት ይተረጉመዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግን ከዚህ ትርጉም በላይ ነው፤ እርሱ የሕዝብ ልጅ፣ የሀገር ፍቅር ነጸብራቅ፣ የቃል ኪዳን ታማኝ ነው።
ጀግናው ሠራዊታችን ከሀገር አልፎ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የከፈለውን መስዋዕትነት ታሪክ በወርቃማ ቀለም ዘግቦታል።
ከ60 ዓመታት በፊት በኮሪያ ጦርነት ያሳየው እፁብ ድንቅ ጀግንነት፣ በኮንጎ እና በሩዋንዳ ዘመቻዎች ያስመዘገበው ገድል እንዲሁም በጎረቤት ሀገራት በሶማሊያ እና በሱዳን ያከናወናቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የዚሁ ታሪካዊ ብቃቱ ሕያው ምስክሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች ሀገሪቱን ለማዳከም አሁንም ይሞክራሉ። ነገር ግን ሠራዊቱ ባዕዳንን እና ባንዳዎችን የሽንፈት ካባ አልብሶ አሳፍሮ የመመለስ ረቂቅ ጥበብ አለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት እንደገለጹት “የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የዓለም እና የአካባቢያችንን ወቅታዊ ሁኔታ ብሎም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ኀይል እንዲኖረን እንሠራለን” ብለዋል።
በቀጣናችን የአየር የበላይነት ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ ትገነባለች። የሚኖረን መከላከያ ዘመናዊ፣ ፈጣሪ፣ ሁሌም ዝግጁ፣ ብቁ እና ንቁ፣ በየአውዶቹ የመሰማራት አቅም እና ቁመና ያለው ይኾናል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ችግሮች ሳይፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ማወቅ እና መግታት፣ ከመጡም መከላከል፣ ከባሰም እንደ አባቶቹ እና እንደ ልማዱ ማሸነፍ የሚችል ኀይል ኾኖ ይገነባል ብለዋል።
ዛሬም በጠላት ኅይል የማትናወጠው እና የማትሸበረው ኢትዮጵያ በልጆቿ ብርቱ ክንድ ወደፊት ትጓዛለች። ትናንት በጽናት አልፋለች፤ ዛሬም ፈተናዎችን በልማት፣ በአንድነት እና በሠራዊቷ ጀግንነት እያሸነፈች ትራመዳለች። ነገም ቢኾን ጠላቶቿን እያሳፈረች፣ ሉዓላዊነቷን አስከብራ፣ የታሪኳ እና የጽናቷ ባለቤት እንደኾነች በከፍታ እና በክብር ጉዞዋን ትቀጥላለች።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየደፈሯትን ሁሉ እያንበረከከች በጽናት የቆመች ሀገር፤ ኢትዮጵያ !