
ዓለም በኃያላን አምባገነንነት እና በቅኝ ግዛት ደመና በተሸፈነችበት በዚያ ዘመን የራሷ ሥርዓተ መንግሥት፣ የራሷ ፊደል፣ የራሷ የነጻነት አየር ያላት አንዲት የጽናት ሀገር ነበረች፤ ኢትዮጵያ
ይህች ምድር የደፈሯትን ሁሉ ያንበረከከች፤ የተመኟትን ያሳፈረች፤ የታሪክን አቅጣጫ በቀለም ሳይኾን በደም እና በወርቃማ ጽናት የቀየሰች የነጻነት ተምሳሌ ናት።
ወደ ኋላ መለስ ብለን የታሪክን ገጾች ብንገልጥ፤ የዓባይ ገዥነትን ተመኝተው፤ የቀይ ባሕርን በር ሰብረው ኢትዮጵያን ሊያንበረክኩ የመጡት የወቅቱ የግብፅ ወራሪዎች በጉንደት እና በጉራዕ ተራራዎች ላይ ያጋጠማቸው ሌላ አልነበረም።
የኢትዮጵያ ልጅ ሀገሩን ሲደፍሩበት የሚያሳየውን እሳት አላወቁትም ነበር፤ የከዲቭ እስማኤል ዘመናዊ እና በምዕራባውያን የተገነባ ጦር በኢትዮጵያ ተራራዎች መካከል አፈር በላ፤ የመጣበትን ሕልም አጥቶ ወደኋላው ተመለሰ።
ኢትዮጵያ ድንቅ የኾነውን የታሪክ ትምህርት ለወራሪዎች አስተማረች፤ “የእኔን ወሰን የደፈረ ይበላል” የኢትዮጵያውያን የሕይወት መርሕ ነው።
የዓለም ኃያላን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ተካፍለው ሲጨርሱ፣ የመጨረሻዋን ጽኑ ሀገር ለማንበርከክ በ1888 ዓ.ም የፋሽስት ጦር ዘመናዊ መሣሪያውን ደቅኖ ዓድዋ ላይ ደረሰ።
ነገር ግን ዓድዋ የጦር ሜዳ ብቻ አልነበረችም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት መነሻ፤ የጋራ ጽናት መግለጫ እንጂ በእቴጌ ጣይቱ ብልህነት እና በአጼ ምኒልክ መሪነት ከጫፍ እስከ ጫፍ የተመመው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ዘመናዊውን የፋሽስት ሠራዊት በዓድዋ ተራራዎች ስር ድብልቅልቁን አወጣው። ዓድዋ የነጻነት አየር፣ የፓን-አፍሪካኒዝም ጽዋ፣ የጥቁር ሕዝብ እኩልነት አርማ ኾኖ በታሪክ ሰማይ ላይ ዘላለም እንዲበራ አደረገች።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ድል በጦር ሜዳ ብቻ አላቆመም፤ ጥበብ እና ጽናት በባዶ እግርም እንደሚያሸንፉ ዓለም የተገነዘበችው በ1952 ዓ.ም በሮም ከተማ ነበር። በጣሊያን እምብርት በሮም ጎዳናዎች ላይ አንድ ቀጭን፣ ረጅም፣ የጽናት ምሳሌ የኾነ ኢትዮጵያዊ በባዶ እግሩ ይሮጥ ነበር። ሻምበል አበበ ቢቂላ።
ሻምበል አበበ ቢቂላ ጣሊያኖች ሀገሩን በወረሩበት እና በበደሉበት ምድር ላይ የሮምን ታሪካዊ ፍርስራሾች አልፎ የመጨረሻዋን መስመር በመጀመሪያነት ሲያቋርጥ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በሮም ሰማይ ላይ ከፍ ብሎ ተውለበለበ።
አበበ ቢቄላ በባዶ እግሩ ሮጦ የዓለምን ዘውድ ሲጭን፣ ኢትዮጵያ በስፖርት እና በጥበብ መድረክ ጭምር እንዴት እንደምታንበረክክ ለዓለም አበሰረ።
ዛሬስ? ያ የትላንት የድል እና የእምቢተኝነት መንፈስ አልቀጠለምን? ልትሉ ትችሉ ይኾናል። ዛሬ ድላችን የጦር ሜዳ ብቻ አይደለም፤ የልማት እና የዲፕሎማሲም እንጂ በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ ዓድዋ፤ የዚህ ትውልድ የጽናት ፍሬ ነው።
የውጭ ጫናዎች፣ የዲፕሎማሲ ማዕበሎች እና የኢኮኖሚ ፈተናዎች ቢደቀኑብንም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ክንድ እና ላብ ተፈጥሮን አሸንፈው ብርሃንን ለምድራቸው አብሰረዋል።
በዲፕሎማሲው መድረክም ቢኾን ከመንግሥታት ሊግ ( ከተባበሩት መንግሥት ድርጅት) እስከ አፍሪካ ኅብረት መሥራችነት፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነት እና ጥቅም ሳታስደፍር፣ የአፍሪካን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረክ ማስከበሯን ቀጥላለች።
በዘላለም አስፋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
