ሚኒስትርነት ማቀድ ብቻ ሳይኾን መፈጸም ጭምር ነው።

8
ሀገር በሥልጣኔ ማማ ላይ እንድትቀመጥ፤ የኢኮኖሚ ስኬቶች እንዲመዘገቡ፤ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች እንዲበለጽጉ እና የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በሀገሪቱ በሥራ ኀላፊነት ደረጃ የሚቀመጡ ግለሰቦች ወሳኝነት አላቸው።
በኅላፊነት ደረጃ የሚቀመጡ መሪዎች ሙስናን መዋጋት፤ ሰላም እና ልማትን ማረጋገጥ፤ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም፤ የሕዝብን ጥቅም ማረጋገጥ፤ በዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት፤ ሀገርን ተወዳዳሪ ማድረግ እና ሌሎች ተግባራትን ከሕዝብ ጋር በመኾን መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።
የሀገር ስኬትን ለማስቀጠል በሕዝብ ድምጽ የሚመረጥ መንግሥት አዲስ መዋቅርን ይፈጥራል። የሥራ አሥፈጻሚ ካቢኔውን በመምረጥ የሥራ ኀላፊነት ሹመትን ይሰጣል።
በኢትዮጵያም በሕዝብ ድምጽ የተመረጠው የመደመር መንግሥት የሀገርን ሥልጣኔ ያስቀጥላሉ፤ የኢኮኖሚ እድገትን ያስመዘግባሉ፤ የሕዝብን ጥቅም ያስቀድማሉ ያላቸውን ሚኒስትሮች መርጦ ሾሟል።
በሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ሥብሠባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሚኒስትሮችን ለሹመት ባቀረቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት የማጽናት እና የማስቀጠል ፍላጎቱን 54 ሚሊዮን ዜጎች በምርጫ በመሳተፍ ከፍተኛ አደራ ማስቀመጣቸውን ገልጸዋል።
የሕዝብን አደራ መሸከም የሚያስችል ትከሻ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት። ሚኒስትሮች ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ ታላቅ ኀላፊነት መኾኑን የሚገነዘቡ፤ መወጣት የሚችሉ፤ ሕዝብ አብዝቶ የሚጠይቀውን ሙስናን የሚጠየፉ እንዲኾኑ ተሠርቷል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ እድገት፤ ለውጥ እና መሻሻል እያንዳንዱን ዜጋ የማይነካ ከኾነ ዋጋ የለውም ነው ያሉት። ሚኒስትሮች ከፍተኛ የሕዝብ አደራ የተጣለባቸው መኾኑን ገልጸዋል።
“ሚኒስትሮች መሾም ሸክም መኾኑን እንዲገነዘቡም” አሳስበዋል። ሹመት የምንዝናናበት ሳይኾን የምንሠራበት፤ ኢትዮጵያን ለማጽናት፤ ለማበልጸግ ወደ ሥልጣኔ ጉዞ ለማስኬድ ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት የሥራ መስክ መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
📌 ከሚኒስትሮች በቀጣይ ምን ይጠበቃል? ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሚኒስትሮች ሹመት ወቅት በንግግራቸው በሥልጣን ወቅት አገልጋይ መኾን፤ እጅ እና ልብን ንጹሕ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ሚኒስትሮች ጠንክሮ መሥራት ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ አመላክተዋል።
ሚኒስትርነት ማውራት፤ ማቀድ ብቻ አይደለም መፈጸም፤ ማሥተባበር እና መሸከም ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአባትነት ሥነ ልቦና መላበስ ያስፈልጋል ብለዋል።
የእኛ መሻት የሠለጠነች፤ ዜጎቿን የሚነካ የልማት እንቅስቃሴ የምታደርግ፤ ለሁሉ እኩል የኾነች፤ ሁሉ የእኔ የሚላት እና የሚሠራላት ሀገርን መገንባት ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በ2019 በጀት ዓመት አዳዲስ አሠራሮችን መከተል ከምንጊዜም በላይ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የሥራ ኀላፊዎች የሕዝብን ፍላጎት ያስቀደሙ፣ የዛሬን እና የወደፊት ራዕያችንን ጭምር የሚመለከቱ፣ ጊዜን እንደ አንጡራ ሃብት የወሰዱ፤ ፋይዳውን ከፍ አድርገው የሚረዱ፤ የዋዛ ፈዛዛ ልምምድን የሚጠየፉ እና ትጋት ያላቸው አገልጋዮች እንዲኾኑ አመላክተዋል። የሕዝብን ድምጽ በታላቅ አደራ በብቃት፤ በታማኝነት፤ በንጽሕና እና በቁርጠኝነት መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የክልሉን የሰው ኀይል በቴክኖሎጂ ለማብቃት እየተሠራ ነው” ፕሮፌሰር ማተብ ታፈረ
Next articleየደፈሯትን ሁሉ እያንበረከከች በጽናት የቆመች ሀገር፤ ኢትዮጵያ !