“የክልሉን የሰው ኀይል በቴክኖሎጂ ለማብቃት እየተሠራ ነው” ፕሮፌሰር ማተብ ታፈረ

4
የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ ዲጂታል እና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ጋር የኤአይ ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችል የጋራ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ማተብ ታፈረ እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዋነኛ ትኩረት ቴክኖሎጂ ነው። የተደረገው የውል ስምምነትም ዩኒቨርሲቲው ለክልሉ መሪዎች እና ሙያተኞች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ዘርፍ ተጨባጭ አቅም ለመፍጠር የሚያስችለው መኾኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የክልሉን ችግሮች በመለየት እና በመፍታት ረገድ አቅሙን የሚያሳድግ ተቋም መኾኑን ጠቁመዋል። የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የውል ማጠናቀቂያ ብቻ ሳይኾን ከተቋሙ ጋር በቅርብ በመሥራት የተጀመረውን የሥልጠና መርሐግብር አጠናክሮ ለማስቀጠል እና በዘላቂነት የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት የሚያስችል መኾኑን አብራርተዋል።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የዘመኑ ችግር ፈቺ ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ትኩረት ያገኘ ቴክኖሎጂ በመኾኑ የሰው ኀይልን ለማጠናከር ከፍተኛ አጋዥ መሣሪያ እንደኾነም ተናግረዋል።
ከአካዳሚው ጋር በጋራ በመሥራት ለክልሉ ባለሙያዎች እና መሪዎች በቴክኖሎጂ ዕውቀት ለመገንባት እና ለሀገር የላቀ አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚሠራም አስረድተዋል።
የአፍሪካ ዲጂታል እና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፕሮፌሰር ሸጋው መንግሥቴ አካዳሚው ከአቅም ግንባታ ጋር በተያያዘ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ)፣ በብሎክቼይን፣ በሳይበር ሴኪዩሪቲ እና በዳታ አናሊቲክስ ዘርፎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የመንግሥት፣ የቢዝነስ እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን አቅም ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኤአይ ቴክኖሎጂ ማዕከል በክልሉ መቋቋሙ የሰው ኀይልን ለማብቃት፣ የክልሉ ተቋማት በቴክኖሎጂ ተጠናክረው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እና ለውጥ የሚያመጣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ወደ ሀገሪቱ እንዲገባ ለማገዝ ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም ብቻውን በቂ ሳይኾን ከክልሉ ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው የሰው ኀይል በቴክኖሎጂ እንዲበቃ በጋራ እንደሚሠሩም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ የሰው ልጅን አቅም በማጎልበት እና በመደገፍ ሥራዎችን በቀላሉ፣ በፈጣን ሁኔታ፣ ጊዜን እና ጉልበትን በቆጠበ መልኩ ለማከናወን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ሥራው ድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“እምቅ ሃብትን በዘመናዊ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleሚኒስትርነት ማቀድ ብቻ ሳይኾን መፈጸም ጭምር ነው።