“እምቅ ሃብትን በዘመናዊ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

3
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ “ዘመናዊ ግብርና ለሁለንተናዊ ልዕልና” በሚል መሪ መልዕክት በጎንደር ከተማ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) እንደገለጹት የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ የረጅም ዘመን የዕድገት መሠረት ቢኾንም እስካሁን በሚፈለገው ልክ ማደግ አለመቻሉ ትልቅ ተግዳሮት ኾኖ ቆይቷል።
ሀገራዊ ዕድገትን ለማፋጠን ዘርፉን ማዘመን ከመሪዎች እና ከባለሙያዎች የሚጠበቅ ዋነኛ ተግባር መኾኑን አስረድተዋል። የጎንደር ቀጣና ለሀገር ዕድገት የሚኾኑ ምርቶች የሚመረቱበት በመኾኑ ለውጤታማነቱ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተለይም እንደ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ እና ጥጥ ያሉ ምርቶችን እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እምቅ ሀብትን በዘመናዊ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) የግብርናው ዘርፍ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች ታግዞ ምርታማነቱ ካላደገ የኢንዱስትሪውን አብዮት መደገፍ እንደማይቻል ተናግረዋል።
በክልሉ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ገደማ መሬት በመስኖ የመልማት አቅም ቢኖርም ዘርፉ ባለመዘመኑ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ማልማት አለመቻሉን ገልጸዋል። ለውጤታማነቱ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ መልእክት፦
Next article“የክልሉን የሰው ኀይል በቴክኖሎጂ ለማብቃት እየተሠራ ነው” ፕሮፌሰር ማተብ ታፈረ