“አዲሱ የሹመት አወቃቀር ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ሀገር መኾኗን መሠረት ያደረገ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

15
ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ሥብሠባውን አካሂዷል። ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ያቀረቧቸውን ሚኒስትሮች ሹመት አጽድቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አዲሱን የመደመር ካቢኒያቸውን ሲያዋቅሩ የአሥፈጻሚ አካላት አሠራር ከዝምድና እና ከወገንተኝነት የጸዳ፣ በብቃት እና በሕዝብ ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ መኾኑን ተናግረዋል።
አደረጃጀቱ የዴሞክራሲን እና የመልካም አሥተዳደር መርኾዎችን በማስቀደም፣ ሚኒስትሮች ለሚሠሩት ሥራ ሙሉ ኀላፊነት እንዲወስዱ እና ተጠያቂ እንዲኾኑ የሚያስገድድ መኾኑን ገልጸዋል። ጥብቅ ክትትል እና ግምገማ እንደሚደረግ፣ ክፍተቶች ሲገኙም ሕጋዊ እርምት እንደሚወሰድም አስጠንቅቀዋል።
የካቢኒውን ስብጥር የብሔር፣ የጾታ እና የሃይማኖት ሚዛንን ፍጹም በኾነ ሁኔታ ማሟላት ፈታኝ መኾኑን ተናግረዋል። በተለይ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ የተሠራውን በመልካም ጎኑ አንስተዋል።
አዲሱ የሹመት አወቃቀር ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ሀገር መኾኗን መሠረት ያደረገ መኾኑንም አስገንዝበዋል። ሀገራዊ አንድነትን በማጎልበት እና በጋራ በመቆም ሀገሪቱን ወደተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
✍️ በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleምክር ቤቱ የሚኒስትሮችን ሹመት አጸደቀ።
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ መልእክት፦