“የሕጻናት የዛሬ ጤና የአፍሪካ የነገ ዐቅም ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

26

 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሥርዓተ ምግብ አመራር የልምድ ልውውጥ መድረክን አስጀምረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሥርዓተ ምግብ አመራር የልምድ ልውውጥ መድረክን ከናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ እና ከፍተኛ ልዑካናቸው ጋር አስጀምረናል ብለዋል።

የአፍሪካን ነገ ለመቀየር የሕጻናትን ጤና ማረጋገጥ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በስትራቴጂካዊ አጋርነት የተሣሠሩ ናቸው፤ የሁለቱ ሀገራት ሰፊ የሕዝብ፣ የሰው ሀብት እና የኢኮኖሚ ዐቅም በተቀናጀ ጥረት ሲመራ ለአፍሪካ ዕድገት እና ብልጽግና ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት። ናይጄሪያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን ያመጣነውን ተጨባጭ ተሞክሮ ለመቅሰም ያደረገችው ጉብኝትም የዚህ አጋርነት ተጨባጭ መገለጫ ነው ብለዋል።

ሥርዓተ ምግብ የጤና ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሰው ሀብት ልማት፣ የትምህርት ውጤት፣ የምርታማነት ዐቅም እና የወደፊት ብልጽግና መሠረት ነው። ስለዚህ የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ በከፍተኛ የፖለቲካ አመራር፣ በተቀናጀ የመንግሥት ሥራ እና በተጠያቂነት መመራት ይገባዋል።

ባለፉት 10 ዓመታት በሰቆጣ ቃል ኪዳን የጀመረችውን ጉዞ በጠንካራ ፖለቲካዊ አመራር፣ በተቋማዊ አሠራር፣ በየደረጃው በሚደረግ ክትትል እና በተቀናጀ የበጀት ምደባ በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግባለች።

የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የመሪዎች የልምድ ልውውጥ ይህን ተሞክሮ ከማካፈል ባለፈ የሁለቱን ሀገራት አቅም በማቀናጀት ለጤናማ፣ ምርታማ እና ብልጽግናዋን ለምታረጋግጥ አፍሪካ የጋራ መፍትሔ ለመፍጠር ዕድል ይከፍታል።

የሕፃናት የዛሬ ጤና የአፍሪካ የነገ ዐቅም ነው። በዚህ እምነት የሁለቱን ሀገራት ትብብርና የመሪዎችን ቁርጠኝነት በማጠናከር፣ ለጤናማና ምርታማ ትውልድ ጠንካራ መሠረት እንጥላለን ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

#የመደመር_መንግሥት

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ 🇪🇹🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_27_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሌብነት እና ሙስናን በመታገል የሕዝብን እምነት ማትረፍ ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ
Next articleአቶ ታምራት ደምሴ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኾነው ተሾሙ።