ከክፍል ጥናት እስከ ትልቅ ሙዚየም- የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጉዞ! 🏛️🇪🇹

5

 

ዩኒቨርሲቲዎች ትውልድን በዕውቀት ከማነጽ ባሻገር የአንድን ማኅበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ፣ ባሕል፣ ታሪክ፣ ማኅበራዊ መገልገያዎችን በጥናት እና ምርምር በመደገፍ ለማስተዋወቅ ይሠራሉ።

የሀገር ባሕላዊ እሴቶች እንዲቀጥሉ፤ አብሮነት እንዲጠነክር እና የሀገሩን ጥቅም የሚያስቀድም ትውልድ እንዲፈጠር ይተጋሉ። የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲም የአካባቢውን ማኅበረሰብ የባሕል መገለጫዎች ለትውልድ ለማስተላለፍ እየሠራ ይገኛል።

በዩኒቨርሲቲው የአገው ጥናት ኢንስቲትዩት የሙዚዬም እና ኤግዚቪሽን ባለሙያ እንግዳየሁ እሱነህ ሙዚዬሙ የአገውን ሕዝብ ቋንቋ፣ ባሕል እና ታሪክን በሳይንሳዊ መንገድ አደራጅቶ የያዘ ነው ብለዋል።

በሙዚዬሙ ውስጥ የአገውን ሕዝብ የአኗኗር ዘይቤ የሚገልጹ በጥናት የተደገፉ ጽሑፎች እና በማኅበረሰቡ ጥቅም ላይ የሚገኙ ቁሳቁስ እንደሚገኙበት ነው ያነሱት።

የአገው ሕዝብ በስፋት የሚጠቀምባቸው እንደ ጭራ፤ የአገው ጥላ እና መሠል ቁሳቁስ በሙዚዬም መቀመጣቸውን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ዓላማ ባሻገር የአካባቢውን ባሕል፣ ቋንቋ፣ ቅርስ እና ታሪክ ለትውልዱ ለማስተላለፍ ሙዚዬሙ እንደተቋቋመ ነው ያነሱት።

ሙዚዬሙ ስለ አገው ሕዝብ አኗኗር፣ ታሪክ እና ባሕል ጥናት እና ምርምር መሥራት ለሚፈልጉ ተመራማሪዎች የመረጃ ምንጭ ኾኖ እንደሚያገለግልም ገልጸዋል።

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአገው ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ብርሃኑ አሳዬ የሙዚዬሙ ዓላማ እየጠፉ ያሉ የጥንት መገልገያ ቁሳቁስ በማሠባሠብ ለመማር ማሥተማር አገልግሎት ማዋል ነው ብለዋል።

ከመማር ማሥተማር አገልግሎት ባሻገር የጥንታዊ የማኅበረሰቡ መገልገያዎችን አሠራር እና ጥቅም በጥናት እና ምርምር በመለየት፣ በምርምር ውጤት ላይ በመነሳት ወደ ማኅበረሰብ አገልግሎት ተደራሽ እንዲኾኑ እና ማኅበረሰቡ በድጋሜ እንዲጠቀማቸው ማስቻል መኾኑን ተናግረዋል።

የዕደ ጥበብ ሥራዎችን፤ የሸክላ አሠራርን፤ የፈረስ መዋቢያ ቁሳቁስ በተመለከተ ለወጣቶች ሥልጠና በመሥጠት እና እንዲያመርቱ በማስቻል የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የማኅበረሰቡን የዕደ ጥበብ ሥራዎችን በማስቀጠል በዲጂታል መተግበሪያዎች በማስተዋወቅ የዓለም ሕዝብ እንዲያውቃቸው እና እንዲጠቀማቸው ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሙዚዬሙ የአገው ሕዝብ ታሪክ ብቻ የሚሠንድ ሳይኾን የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ባሕል ታሪክ በሙዚዬሙ በመሠነድ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ላይ ያለመ መኾኑን ነው ያነሱት።

ከአቻ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የሀገር ባሕል እና ታሪክ መገለጫ ቁሳቁስ ለመሠነድ ይሠራል ነው ያሉት።
ስፋት ያለው የሙዚዬም ማዕከል ለመገንባት በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።

#የመደመር_መንግሥት

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ፣ #ታላቅ_ርዕይ 🇪🇹🇪🇹

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

#ባሕር_ዳር #መስከረም_27_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከእሳት ፈተና እስከ ሰማይ የበላይነት፤ በቴክኖሎጂ የዘመነው የብረት አሎሎ።
Next article“ሌብነት እና ሙስናን በመታገል የሕዝብን እምነት ማትረፍ ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ