ከእሳት ፈተና እስከ ሰማይ የበላይነት፤ በቴክኖሎጂ የዘመነው የብረት አሎሎ።

27

 

እሳት በፈተነው የታሪክ እቶን አልፎ በጽናት እና በደም በተፃፈ መስዋዕትነት የቆመ ሠራዊት የሀገር ሕያው ዘብ ነው።

“ዱሩ ቤቴ፣ ድንጋዩ ትራሴ፣ እናት ሀገሬ ሕይወቴ” ብሎ በሀሩር እና በቁሩ፣ በዝናብ እና በውርጩ የታገለው ይህ የሀገር መድኅን የዘመናት ፈተናዎችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ የሀገረ-መንግሥቱን ሕልውና እና የሉዓላዊነት መሠረት አጽንቶ ይገኛል።

በታሪኩ ሂደት ለሀገሩ ካለው ጥልቅ ፍቅር እና ታማኝነት የተነሳ ከጀርባው የተወጋበት፣ በገዛ ሀገሩ አፈር ላይ እንደ ባይተዋር የተገፋበት፣ የጽናት እና የአይደፈሬነት ክብሩን ገፈው የውርደት ማቅ ሊያለብሱት እኩይ ሴራ የተሸረበበት ጥቁር የታሪክ ምዕራፍንም አሳልፏል

ይሁን እንጂ ሀገርን አጥር አልባ እና ድካም የበዛባት ለማድረግ አልመው የተነሱ አካላት ምኞት ቅዠት ኾኖ ቀርቷል። ሠራዊቱ በፈተና እሳት አልፎ የጸና የብረት አሎሎ ኾኖ በመውጣት፣ ከአንድ ፓርቲ ርዕዮተ-ዓለም የተላቀቀ፣ ለሕገ-መንግሥቱ እና ለሀገራዊ ሉዓላዊነቱ ብቻ የቆመ እና የሙያ ልህቀቱ የጎላ ብሔራዊ ጦር ኾኖ ዳግም ተወልዷል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት የተገነባው ግዙፍ የወታደራዊ አቅም የዛሬን ፈተና ማሸነፍ ብቻ ሳይኾን የነገዋን ዓለም የኀይል አሰላለፍ የሚወስን እና ስጋቶችን ቀድሞ የሚያነብ የላቀ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ፍሬ ነው።

ዛሬ ሠራዊቱ ምድር ላይ በሚተመው እግረኛ ጦር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሳይኾን በዘመኑ ረቂቅ ቴክኖሎጂ የተቃኘ ግዙፍ ኅይል ለመኾን በቅቷል።

የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ቀጣና ያለው የኀይል ፍጥጫ እና የጂኦፖለቲካ ውጥረት ሀገሪቱን የማይበገር የመከላከያ ኃይል እንድትገነባ አስገድዷታል፦

በተለይም ዘመናዊ የጦር ጄቶች፣ የላቁ ድሮኖች፣ ፀረ-ድሮኖች፣ የውጊያ ሄሊኮፕተሮች እና ዘመናዊ ራዳሮች በመታጠቅ የአየር ክልሉን ወደማይደፈር ምሽግ ቀይሮታል።

የምድር ኃይሉ በመካናይዝድ፣ በኮማንዶ፣ በአየር ወለድ እና በሪፐብሊካን ጋርድ በዘመናዊ እዝ ተቀይሯል። የትኛውንም የመካናይዝድ ኀይል ዶጋመድ የሚያደርጉ ድሮኖች እና ተተኳሾች በሀገር ልጆች አዕምሮ እና እጅ እየተመረቱ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት “ኢትዮጵያ ትላንት አልተደፈረችም፣ ነገም አትደፈርም! በክብር እና በነፃነት ለትውልድ የምትሻገር ብቸኛዋ የአፍሪካ ፈርጥ ኾና ትቀጥላለች።

“የእኛ ዝግጅት በድፍን አፍሪካ ሰላም እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ በቀጣናችን ላሉ ሀገራት አለኝታ፣ መከታ እና ጋሻ ለመኾን ነው” ብለዋል።

በመኾኑም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪካዊ ጽናቱን ከዘመናዊ የቴክኖሎጂ ልህቀት ጋር አዋህዶ የገነባው ይህ አዲስ አቅም የሀገርን ሉዓላዊነት አስተማማኝ አጥር የሚያደርግ ብቻ ሳይኾን በቀጣናው ሰላም እና ሕልውና ላይ የሚቃጡ ስጋቶችን ሁሉ የሚያከሽፍ ድልድይ ኾኖ ይቀጥላል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_27_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቅ አዋጅ ላይ እየተወያየ ነው።
Next articleከክፍል ጥናት እስከ ትልቅ ሙዚየም- የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጉዞ! 🏛️🇪🇹