
7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ እያካሄደው በሚገበው 1ኛ ልዩ ስብሰባው በፌዴራል መንግሥት አሥፈጻሚ አካላት ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ እየመከረ ይገኛል።
የምክር ቤት አባል እና የመንግሥት ተወካይ የኾኑት ፍቃዱ ተሰማ ከዚህ በፊት በነበሩት 22 አሥፈጻሚ አካላት ላይ የቁጥር ልዩነት እንደሌለ እና ከቁጥር አንጻር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በነበሩበት 22 ኾነው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ይህም ኾኖ በሁለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ ብቻ የስያሜ ለውጥ መደረጉን እና ሁለት ሚኒስቴሮች አንደ አዲስ መቋቋማቸውን አብራርተዋል።
እንደ አዲስ የተቋቋሙት ሁለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ቀድሞ “የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር” የነበረው እና ቀድሞ “የቱሪዝም ሚኒስቴር” የነበረው በአዲሱ “የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር” በሚል መቋቋማቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ቀድሞ “የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር” የነበረው “የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር” በሚል እና ቀድሞ “የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር” የነበረው “የሎጀስቲክስ ሚኒስቴር” በሚል ስያሜያቸው መቀየሩ ተገልጿል።
በሚኒስቴር መሥራያ ቤቶቹ ላይ ማሻሻያው ያስፈለገበት ምክንያት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እና ከተልዕኳቸው ጋር ለማጣጣም መኾኑም ተብራርቷል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ለምክር ቤቱ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
