በሳምንት 230 ሺህ ጫጩት በማስፈልፈል ለገበያ ለማቅረብ የተዘጋጀው የኮምቦልቻ ዶሮ ሃብት ልማት ኢንተርፕራይዝ

4

 

የኮምቦልቻ ዶሮ ሃብት ልማት በክልሉ በዶሮ ሃብት የሚስተዋለውን የጫጩት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት

በመንግሥት ደረጃ ከተቋቋሙት ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው። ድርጅቱ በተለይም የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን እያስፈለፈለ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል።

የኮምቦልቻ ዶሮ ሃብት ልማት ኢንተርፕራይዝ ሥራ አሥኪያጅ ታደሰ አሕመድ (ዶ.ር)ለአሚኮ እንደተናገሩት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጉዳት ደርሶበት ሥራው

ተስተጓጉሎ እንደነበር አንስተዋል። የክልሉ መንግሥት ባደረገው 100 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አማካኝነት እንደገና ተቋቁሞ ወደ አገልግሎት ተመልሷል።

ተቋሙ 226 ለሚኾኑ ዜጎች በቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅት ዋነኛ የጫጩት ስርጭት ማዕከል በመኾን ለሌማት ቱርፋት መርሐ ግብር አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ሥራ አሥኪያጁ እንዳብራሩት ኢንተርፕራይዙ ጥምር ጥቅም የሚሰጡ እና የተሻሻሉ ከአንድ ቀን ጫጬት እስከ ሦሥት ወር ዕድሜ ያላቸው የዶሮ ዝርያዎችን በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

በማንኛውም የአየር ሁኔታ ተላምዶ ምርት መስጠት የሚችሉ የ”ቴትራ ኤች” ዝርያ እንዲኹም “ኮይኮይክ”

የተባሉ የዶሮ ዝርያዎችን በማስፈልፈል ያሠራጫል። በሳምንት እስከ 60 ሺህ ጫጩቶችን እያስፈለፈለ ወደ

ገበያ ሲያቀርብ የቆየው የኮምቦልቻ ዶሮ ሃብት ልማት ኢንተርፕራይዝ አሁን ደግሞ 230 ሺህ ጫጩት በማስፈልፈል ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን አብራርተዋል።

እንደ ሥራ አሥኪያጁ ገለጻ ተቋሙ በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ለሚገኙ ዶሮዎች የሚኾን የተመጣጠነ መኖ

እያመረተ ያቀርባል። በተጨማሪም ለወተት ምርት እና ለከብት ማድለብ የሚኾን የተመጣጠነ መኖ በማምረትም ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ አብራርተዋል።

ስድስት አይነት የዶሮ በሽታ መከላከያ ክትባቶችን ለአርቢዎች እና ለአሳዳጊዎችም እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ተቋሙ በዘርፉ ለተሠማሩ አርቢዎች የሥልጠና እና የማማከር አገልግሎትም ይሰጣል።

አገልግሎቱን ለማስፋት ታቅዶ በ40 ሚሊዮን ብር አዲስ የማስፈልፈያ ማሽን ማስገባታቸውንም አንስተዋል። በዚህም ምርቱን ለማሳደግ ሙሉ ዝግጅት ተጠናቅቋል ነው ያሉት።

ተቋሙ ጫጩት የማቅረብ ችግር እንደሌለበት ያረጋገጡት ሥራ አሥኪያጁ በተለይም የአካባቢው ማኅበረሰብ ጫጩት በመውሰድ እና የተመጣጠነ መኖ ከተቋሙ በማግኘት ተጠቃሚ እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_27_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከሰብል ሥብሠባ እስከ ጎተራ፤ ለምርት ጥራት ዘመናዊ አሠራርን መተግበር !