
በአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለተኛው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የዳኞችን የሙያ አቅም ለማጎልበት፣ ተጨማሪ ንባብ እና ጥናቶችን ለማስፋፋት እንዲሁም የጋራ ተቋማዊ ግንዛቤን ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥልጠናዎች፣ ገለጻዎች እና ውይይቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።
በዕለቱ የጉባኤ ውሎ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ትግበራ ሂደት፣ የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ ሕጎች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ አቤቱታ አቀራረብ እና ሙግት መመሪያ ረቂቅ ላይ ገለጻ እና ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር መኳንንት አገአሁ (ዶ.ር) በክልሉ ፍርድ ቤቶች በተከናወኑ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ላይ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።
እንደ ዶክተር መኳንንት ገለጻ የቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገት የሰዎችን፣ የተቋማትን እና የሥራ አሠራሮችን እንቅስቃሴ በፍጥነት እየቀየረ በመኾኑ ፍርድ ቤቶችም የዚሁ ለውጥ አካል መኾን አለባቸው።
በተለይም ዲጂታላይዜሽን የዳኝነት አገልግሎትን ተደራሽ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ከማድረጉም በላይ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የፍርድ ቤቶችን የዲጂታላይዜሽን ሥራ በሥርዓት ለመምራት የዲጂታላይዜሽን ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ፍኖተ ካርታው የትኞቹ የፍርድ ቤት ሥራዎች ዲጂታል መኾን እንዳለባቸው እና የአፈጻጸም አቅጣጫቸውን ለመለየት ማስቻሉን ገልጸዋል።
በአፈጻጸም ደረጃም የኔትወርክ እና የዳታ ማዕከል መሠረተ ልማት ዝርጋታ፤ ዘመናዊ ችሎቶች እና የርቀት ሙግት አገልግሎት፤ የደኅንነት ካሜራዎች ተከላ እና የሶፍትዌር ልማት ሥራዎች መሠረተ ልማቶች እና ሥርዓቶች ተዘርግተዋል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ 14 ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ 27 ወረዳ ፍርድ ቤቶች እና ሁለት ማረሚያ ቤቶች በእነዚህ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ታግዘው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የተዘረጉት የዲጂታል መፍትሔዎችም ባለጉዳዮች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ኾነው አቤቱታቸውን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ እንዲያቀርቡ ያስችላል።
ለዳኞችና እና ለባለጉዳዮች ተዛማጅ መረጃዎች በወቅቱ እንዲደርሷቸውም ያደርጋል። ባለጉዳዮች በስማቸው ወይም በመዝገብ ቁጥራቸው የጉዳያቸውን ሂደት እና ቀጠሮ እንዲከታተሉ ያስችላል። ነው ያሉት።
የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ፣ የድረ-ገጽ አገልግሎቶች፣ የዕውቀት አሥተዳደር ሥርዓት፣ ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት እና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዲጂታል ሙዚየምም ለሥራው ምቹ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ልዩ አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ፣ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ አዋጆች ማሻሻያ እና የኤሌክትሮኒክስ አቤቱታ አቀራረብ እና ሙግት መመሪያ ረቂቆችን አስመልክተው ገለጻ አቅርበዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ የማሻሻያው አስፈላጊነት፣ ረቂቁ የተዘጋጀበት ሁኔታ በአዋጆቹ ማሻሻያ የሚደረግባቸውን አንኳር ጉዳዮች እንዲሁም የተዘጋጁትን ማሻሻያዎች ለተሳታፊ ዳኞች አብራርተዋል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ አቤቱታ አቀራረብ እና ሙግት መመሪያ ረቂቅ አስፈላጊነት፣ ለዝግጅቱ ከተደረጉ ጥረቶች እና ከተጠቀሱ ምንጮች ጋር አያይዘው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በቀረቡት ገለጻዎች እና ማብራሪያዎች ላይ የጉባኤው ተሳታፊ ዳኞች የማጠናከሪያ ሀሳቦችን እና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲኾን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ዓለምአንተ አግደው ለተነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
