
በምሥራቅ አፍሪካ ያለው ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ በፍጥነት የሚቀያየር እና ቀጣናዊ ሀገራት ከጋራ ዕድገት ይልቅ መጠላለፍን ያስቀደሙበት እንደኾነ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ሀሳቡ ተስፋ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
እንደ ኤርትራ ያሉ የሕዝባቸውን ይሁኝታ ያላገኙ እና እውነተኛ የመንግሥትነት ባህርይ የሌላቸው ሀገራት የራሳቸውን አጣዳፊ የውስጥ ችግር ወደጎን በማለት የግብጽን አጀንዳ በመሸከም የኢትዮጵያን ህልውና እና የዓባይ ተፋሰስ መብት ለማደናቀፍ እየሠሩ እንደሚገኙ መምህር ሀሳቡ ተናግረዋል።
በመኾኑም እነዚህ ወገኖች በላኪዎቻቸው አማካኝነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፉበት ዘመን ማክተም እንዳለበትም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመንግሥት ምሥረታው ላይ በመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን በቀጣናው ወሳኝ ሀገር የማድረግ ርዕይ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ መኾናቸውን ገልጸው ይህንን ለማሳካትም የጎረቤት ሀገራትን እኩይ ዓላማ እና የተላላኪነት ሚና በውል የተረዳ የተቀናጀ ዕቅድ መንደፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በራሷ ታሪክ እና ደረጃ ልክ የተጀመሩ አዳዲስ እሳቤዎችን እና ውሳኔዎችን በቆራጥነት ገቢር ማድረግ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ያማከሉ፣ ነገር ግን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ልዕልና የማያስደፍሩ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ተገቢ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ያሉትን ተጽዕኖዎች እና የመውጫ መግቢያ እገዳዎችን ሰብራ በመውጣት በቀጣናው እና በአፍሪካ ደረጃ ወሳኝ ሚናዋን እንድታረጋግጥ ከአዲሱ መንግሥት ቆራጥ እና ተግባራዊ እርምጃዎች እንደሚጠበቁም የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያው አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
