ዲጂታል ቴክኖሎጂ ካመጣው የፋይናንስ ደኅንነት ስጋት ራስዎን እንዴት እየጠበቁ ነው?

11
ባሕር ዳር: መስከረም 27/2019 ዓ.ም (አሚኮ) የዲጂታል ቴክኖሎጂ የፋይናንስ ተቋማትን አሠራር በከፍተኛ አዘምኗል። ከእነዚህም መካከል የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት አንዱ ነው።
ደንበኞች በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ የፋይናንስ ግብይቶችን በስልካቸው ብቻ በሰከንዶች ውስጥ እንዲፈጽሙ በማድረግ ህይወትን አቃሏል።
ነገር ግን ከዚህ ፈጣን እና ዘመናዊ አሠራር ጋር ተያይዞ የሚመጡ የሳይበር ደኅንነት ሥጋቶች እና የገንዘብ ማጭበርበሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ የፋይናንስ ሥጋት ኾነዋል።
እንደ “ኢንተርፖል” (INTERPOL) መረጃ በየዓመቱ በዲጂታል እና በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ምክንያት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚገመት ሃብት ይበዘበዛል።
​✍️ቅድመ ጥንቃቄዎች፦
#ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም፦ ቢያንስ ከ12 በላይ ፊደላት፣ ቁጥሮች እና ምልክቶች (@, #, $) መቀላቀል፣ የልደት ቀን ወይም ሥም አለመጠቀም፣ ምስጢርነቱንም በጥብቅ መጠቀም ይመከራል።
#የተረጋገጠ የኢንተርኔት ግንኙነት መጠቀም፦ የድኅረ ገጽ አድራሻው በ https:// መጀመሩን ያረጋግጡ። ይህም መረጃው መመስጠሩን ያሳያል። የፋይናንስ መረጃዎችን ለማስገባት የሕዝብ ዋይፋይ መጠቀምም ለአደጋ ያጋልጣል።
#የመረጃ ልውውጥ አቅራቢዎችን ማንነት ማረጋገጥ፦ ከባንክ እንደኾነ የሚገልጽ ያልተጠበቀ ጥሪ ወይም የመልዕክት ጥያቄ ሲደርስ መረጃ ከመስጠት መቆጠብ፤ ይልቁንም በባንኩ ይፋዊ ስልክ ቁጥር ደውሎ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ።
#መተግበሪያዎችን ከተረጋገጠ ምንጭ ማውረድ፦ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎችን ከባንኩ ይፋዊ ድኅረ ገጽ ወይም ከታመኑ የመተግበሪያ መደብሮች (Play Store / App Store) ብቻ ማውረድ።
#ተጨማሪ የደኅንነት ማረጋገጫዎችን መጠቀም፦ ሁለት ደረጃ ማረጋገጫ (MFA) ማብራት ይገባል። ይህ ደግሞ ወደ መለያው ሲገቡ ተጨማሪ አጭር የጽሑፍ መልእክት (SMS) ኮድ ይጠይቃል። የጣት አሻራ ወይም የፊት ገጽታ ማወቂያ (Biometrics) ሥልቶችንም መጠቀምም ይመከራል።
​#ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ የባንክ ሒሳብን መፈተሽ፤ ያልታወቀ ወይም አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ከታዩ ወዲያውኑ ለባንክ ማሳወቅም ተገቢ ነው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በንግድ እና ኪሳራ ሕጎች ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ።
Next articleቀጣናዊ መጠላለፍን በመስበር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጥ ይገባል።