
“የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎቱን ማላቅ በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ የሚገኘው የአማራ ክልል የፍርድ ቤት ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬም በተለያዩ የሕግ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እና ገለጻ በማካሄድ ቀጥሏል።
የንግድና የኪሳራ ሕግ ላይ ገለጻ ያደረጉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ ጴጥሮስ የኪሳራ ሕግ በዘመናት ውስጥ ያሳየውን የሕግ እና የፍትሕ እድገት፣ የኪሳራ ሥነ-ሥርዓት ዓላማ እና በአዲሱ የንግድ ሕግ የተካተቱ የሕጉን አጠቃላይ ይዘት በስፋት አብራርተዋል።
የኪሳራ ሕግ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ በሂደት የዳበረ ሲኾን፣ በመጀመሪያ የኪሳራ ሥርዓቶች ትኩረታቸው ባለእዳን መቅጣት እና የአበዳሪዎችን ገንዘብ ማስመለስ ላይ ነበር።
የኪሳራ ሕግ በጊዜ ሂደት ባለእዳን ከመቅጣት ወደ ባለእዳው ንብረት በማሰባሰብ፣ በማሥተዳደር እና ለአበዳሪዎች በፍትሐዊነት በማከፋፈል ላይ ያተኮረ ሥርዓት እየኾነ መጥቷል ብለዋል።
በተለይም የኪሳራ ሕግ ዘመናዊ እድገት ሀቀኛ ነጋዴዎች በንግድ ሥራቸው በሚያጋጥሟቸው የገንዘብ ችግሮች መፍትሔ በመስጠት አዲስ የንግድ ሕይወት እንዲጀምሩ ዕድል የሚሰጥ አቅጣጫ ላይ መድረሱን አቅራቢው አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ በኩልም የ1933 የኪሳራ ሕግ ከቀደምት የሕግ ሥርዓቶች አንዱ መኾኑን ያስታወሱት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ የ1960 የንግድ ሕግ የ1933 የኪሳራ ሕግን በመተካት የኪሳራ ድንጋጌዎችን በራሱ ውስጥ ማካተቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አዲሱ የንግድ ሕግ በኪሳራ ላይ የተለያዩ የመፍትሔ ሥርዓቶችን ማስቀመጡን ተናግረዋል። በተለይም ቅድመ ጥንቃቄ ዕዳን መልሶ ማዋቀር እና መልሶ ማደራጀት ከኪሳራ በፊት የንግድ ድርጅቶች የገንዘብ ችግራቸውን እንዲፈቱ የሚያግዙ ዘመናዊ የሕግ መፍትሔዎች መኾናቸውን አብራርተዋል።
የኪሳራ ሂደት የባለእዳውን ጥቅም ብቻ ወይም የአበዳሪዎችን መብት ብቻ የሚመለከት ሳይኾን የብዙ ወገኖችን መብት እና ጥቅም የሚነካ ስለኾነ በሕግ የተቀመጡ ሥነ-ሥርዓቶችን በጥንቃቄ መተግበር ይጠይቃል።
በመኾኑም የኪሳራ ሥነ-ሥርዓት ዋና ዓላማ ባለእዳን መቅጣት ብቻ ሳይኾን፣ የአበዳሪዎችን መብት በፍትሐዊነት ማስከበር፣ የባለእዳውን ሀብት በሕጋዊ ሥርዓት ማሥተዳደር እና በተገቢው ሁኔታ ለአበዳሪዎች ማከፋፈል እንዲሁም ለሀቀኛ ነጋዴዎች ከኪሳራ በኋላ አዲስ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ሥርዓት መኾኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
