
ለኢትዮጵያ ክብር የሚመጥነው ሰላም፣ መደማመጥ እና አንድነት ነው። ግጭት ለዘመናት አቆርቁዟታል፤ ጦርነት ለዘመናት አድምቷታል። ሀገርን ጦርነት አይሠራትም፤ ግጭትም አያሳድጋትም።
ሀገርን የሚያሳድጋት፣ ከፍ ከፍም የሚያደርጋት ችግሮችን በውይይት መፍታት ነው። ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተነሱ ችግሮች፣ የተፈጠሩ ግጭቶችን ኢትዮጵያን በብዙ ጎድተዋታል። የዕድገቷ ጎታች ኾነውባት ቆይተዋል።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ወደ ግጭት የገቡ ታጣቂዎች ጥያቄዎቻውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ የሰላም አማራጮች ቀርበዋል። ተደጋጋሚ የውይይት በሮች ተከፍተዋል። ብዙዎችም የሰላም ጥሪውን ተቀብለዋል። በተከፈተው የውይይት በርም ገብተዋል።
ነገር ግን አሁንም የጥያቄ መፍቻው ግጭት ነው ብለው የሚያምኑ ታጣቂዎች በየጫካው ሞልተዋል። ለእነዚህም ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እየቀረበ ነው። ምክንያቱም ሀገርን የሚጠቅማት ሰላማዊ የፖለቲካ ባሕል እንጂ ግጭት እና ጦርነት አይደለምና።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ንግግር እነኾ ታሪክ ምርጥ የኾነ ዕድል ከፊታችን ዘርግቷል፤ ኢትዮጵያን ትልቅ ብቻ ሳትኾን ታላቅ የማድረግ ዕድል ተሰጥቶናል። የኢትዮጵያን አዲስ ሥልጣኔ የመገንባት ዕድል በእኛ ዘንድ አለ።
ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ያላት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጸና፣ ምርታማነትን ባሕል ለማድረግ የምትተጋ፣ መሪ እና ፈር ቀዳጅ የኾነች አይበገሬ ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ዕድል ከፊታችን አለ ብለዋል።
ይህንን ታሪካዊ ዕድል ከትጋት ጋር ደምረን እንድንጠቀምበት በጫካ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ወደ ሰላማዊ መንገድ ኑ ነው ያሉት።
ያኮረፋችሁ ወገኖች የይቅርታን መንፈስ ተላብሳችሁ በሀገር ግንባታ ተሳተፉ ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በብሔራዊ ጥቅም ላይ በጋራ ለመቆም እና በአማራጭ ሃሳቦች ለመፎካከር ተነሱ ብለዋል።
የዛሬ ወጣቶች በአርቆ አሳቢነት ነጋችሁን ቅረጹ፤ የትናንት ወጣቶች ካለፈ ስህተታችሁ ተማሩ፣ ከአብዮታዊ የትግል ስልት ራቁ፣ የባንዳነት ልማድን አስወግዱ፣ የተጣሉትን አስታርቁ፣ የሸሹትንም መልሱ ነው ያሉት።
የዛሬ ልጆች በዕውቀት፣ በክህሎት እና በስነምግባር ታንጻችሁ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመውረስ ተሰናዱ፤ የሀገር አባቶች እና እናቶች ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅነት እና ሥልጣኔ ጸልዩ፣ ታሪካችሁን አውርሱ፣ ትውልዱንም ገንቡ ብለዋል።
ሁሉም ዜጋ በተሰፈረለት ጊዜ በላቡ እና በዕውቀቱ የመደመር ሥልጣኔን እውን ለማድረግ ይትጋ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት አልፏል፣ ነገም ገና አልደረሰም፣ ዛሬ ግን ምቹ ኾኖ ቀርቧል፤ ዛሬን ከሠራንበት ትናንትን ማስተካከል ይቻላል፤ ዛሬን ከሠራንበት ነገን መተንበይ ብቻ ሳይኾን የፈለግነውን ዓይነት መንገድ መቅረጽ እንችላለን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ትበልጽጋለች፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፤ ኢትዮጵያ የጠላት ሴራን በጣጥሳ መሻቷን በተግባር ትከውናለች ብለዋል። ሰላማዊ የፖለቲካ ባሕልን ማዳበር፣ ከግጭት እና ጦርነት መራቅ፣ ለጋራ ሀገር በጋራ መሥራት ኢትዮጵያን በብዙ ይጠቅማታል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
