ከማይደፈር ሰማይ እስከ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቀጣይ ጉዞ።

6
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ዓመታት በተካሄደለት ሁሉን አቀፍ የሪፎርም እና የማዘመን ሥራ የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስከብር እና በቀጣናው ተወዳዳሪ የሌለው ዘመናዊ ኃይል መኾን እንደቻለ ተገልጿል።
ይህ ታላቅ መዋቅራዊ ሽግግር በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በሰው ኀይል ልሕቀት እና በሀገር በቀል ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ላይ የተመሠረተ ነው። ከምድር ጦሩ ባሻገር አየር ኀይሉን እና ባሕር ኀይሉን አካትቶ መከናወኑ ደግሞ የሀገሪቱን መከላከያ ኀይል ሽግግር የተሟላ ያደርገዋል።
የኢትዮጵያን አየር ኀይል ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል በማሸጋገር የተራቀቁ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወይም ድሮኖችን በሀገር ውስጥ ማምረት፣ ከባድ መሣሪያዎችን ማደስ እና የጥገና አገልግሎትን እና ሌሎች ተግባራትን በራስ አቅም ማከናወን እንደቻለም ይነገራል።
አካዳሚውን በማጠናከር የራሱን አብራሪዎች እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ከማሠልጠን ባለፈ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የአቪዬሽን ጥገና እና የሥልጠና ድጋፍ መስጠት በመጀመሩ የአህጉሪቱ የልህቀት ማዕከል ለመኾን በቅቷል።
ከሦሥት አሥርት ዓመታት በላይ ያለ ባሕር ኀይል ለመቆየት ተገድዳ የነበረችው ኢትዮጵያ ተቋሙን በዘመናዊ መዋቅር ዳግም ማደራጀት ችላለች። የባሕር ኀይል ጠቅላይ መምሪያ እና ዘመናዊ የማሠልጠኛ ማዕከላት ተገንብተው ሥራ ጀምረዋል። አባላቱ የተራቀቁ የባሕር ላይ ሥልጠናዎችን ወስደዋል።የባሕር ላይ ኮማንዶ ኀይልም እየተደራጀ ነው።
ይህ መዋቅር የሀገሪቱን ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ እና ስልታዊ ጥቅም ለማስከበር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንገግር መንግሥት የወጠናቸውን ትልሞች እና ግቦች ለመከወን ስለሚከተላቸው መፈጸሚያ መንገዶች ሲያብራሩ የኢትዮጵያ መንገድ ምንጊዜም ሁለንተናዊ ኀይልን ማጠናከር መኾኑን ተናግረዋል።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ራስን የመቻል፣ ስትራቴጂያዊ የመከላከል ብቃትን የማሳደግ እና የውስጥ ጥንካሬያችን የሚጸናበት ዘላቂነት ያለው መንገድ ማበጀት ይኾናል ነው ያሉት።
የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ አካላት ጥንካሬ እና አሁን ያለው ተልዕኮን የመፈጸም ብቃት የላቀ እንዲኾን መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ንግግር በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የተጀመረው ይህ የለውጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅነቷን፣ የዓለም እና የአካባቢያችንን ወቅታዊ ሁኔታ ብሎም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ኀይል እንዲኖራት ይሠራል ብለዋል። በቀጣናው የአየር የበላይነትን ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ እንደምትገነባም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ ፈጣሪ፣ ሁልጊዜም ዝግጁ፣ ብቁ እና ንቁ፣ በየአውዶቹ የመሰማራት አቅም እና ቁመና ያለው የመከላከያ ኀይል ይኖራታል ነው ያሉት።
ችግሮች ሳይፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ማወቅ እና መግታት፤ ከመጡም መከላከል፤ ከባሰም እንደ አባቶቹ እና እንደ ልማዱ ማሸነፍ የሚችል ኀይል ኾኖ ይገነባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ከጠመንጃ የበላይነት ወደ ወንድማማችነት”
Next article“በጫካ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ወደ ሰላማዊ መንገድ ኑ”