
ኢትዮጵያ የረጅም ታሪክ ባለቤት እንደመኾኗ መጠን በዘመኗ ባሳለፈችው የሥነ-መንግሥት ታሪካዊ ሂደት ከጥንታዊ የአሥተዳደር ዘይቤ እስከ ዘመናዊ የዴሞክራሲያ ሥርዓት ድረስ ተጠቅማለች ።
በዚህ የቀደመ ታሪክ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ባሕል በአብዛኛው ሕዝብን ያስቀደመ፣ የሕዝብ አሸናፊነትን ያረጋገጠ፣ በጋራ መሥራትን ያገናዘበ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ አልነበረም።
ለሥልጣን በሚደረግ ያልሠለጠነ፤ መሣሪያ ተኮር እና መጠፋፋትን የሚያስከትል የፖለቲካ ባሕል ኢትዮጵያን ብዙ የተማረ ትውልድ አሳጥቷታል።
ይህ አይነቱ ተናጠላዊ፣ ፉክክር የሚበዛበት፣ ግብግብ የሞላበት እና የአሸናፊ ቡድኖች የበላይነት የሚንጸባረቅበት የፖለቲካ ባሕል ብዙ ትውልዶችን የበላ ስለመኾኑ ታሪክ ይነግረናል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት በነበረው በዚህ አይነት የፖለቲካ አካሄድ የሥልጣን ምንጩ ሕዝብ ሳይኾን ቡድን፣ ምርጫ ሳይኾን ጠመንጃ፣ ሀሳብ ሳይኾን ጉልበት ጎልቶ የሚወጣበት ነበር። ለሥልጣን በሚደረግ ትግል የዜጎቿን መራር መስዋትነት ያስከፈለበት የፖለቲካ ታሪክን አሳልፋለች።
ይህንን የፖለቲካ ባሕል ለመቀየር ባለፉት ዓመታት የምርጫ ልምዶች እና ሙከራዎች ቢኖሩም አሸናፊ እና ተሸናፊ ፓርቲዎች በጋራ የመሥራት ልምዶች አልነበሩም።
በተለይም ከመደመር መንግሥት በፊት የነበረው የፖለቲካ አካሄድ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል እንዳይወስኑ የሚያደርግ እንደነበር ይነሳል።
ፓርቲዎችን ለይስሙላ በአንድ ርዕዮተ ዓለም አቅፎ የሚጓዝ ነገር ግን “ዋና እና አጋር”ብሎ የሚከፋፍል ሥርዓት እንደነበርም በቅርብ የነበረው ሥርዓት በአብነት የሚታወስ ነው።
ይህንን የፖለቲካ ባሕል ለመቀየር ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ይገልጻሉ። ልዩነቶች ቢኖሩም ገዢ ፓርቲ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአንድ ሀገር በአንድ መንግሥት ውስጥ አብረው ሊሠሩ እንደሚገባ ያነሳሉ።
ባለፉት አምስት ዓመታት በነበረው የመንግሥት ዘመንም ከወትሮው በተለየ መንገድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር አብረው እንዲሠሩ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።
በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በመንግሥት አሥፈጻሚነት ተካትተው እንዲሠሩ ተደርገዋል። ይህ አዲስ የፖለቲካ ልምምድ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች አረጋግጠዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ የጠመንጃ ባሕልን እና የነፍጥ አዙሪትን በዘላቂነት ማስቀረት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የፖለቲካ ልምምዱ በሰላም፣ በንግግር፣ በዕውቀት እና በመደማመጥ ላይ እንዲመሠረት መንግሥት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ንግግር ባለፉት አምስት ዓመታት “ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መሥራት እንደሚቻል በተግባር አሳይተናል” ነው ያሉት።
በምርጫ ሂደት አሸናፊ እና ተሸናፊ ቢኖርም ኢትዮጵያ ግን አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ዜጋ የላትም ብለዋል። ይህም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ይዞ ለሚመጣ ሁሉ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
በቀጣይም የፖለቲካ ምሕዳሩ በትብብር እና በፉክክር ሚዛን ላይ ተመሥርቶ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል። ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት መንግሥት ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል።
ይህ አዲስ እና የሠለጠነ የፖለቲካ ባሕል የኢትዮጵያ ልጆች ለሥልጣን ሲሉ ደም መፋሰስን፣ መገዳደልን፣ መጠፋፋትን አስቀርቶ ለልዕልናዋ አብሮ መቆምን፣ ለባዕዳን ሀፍረትን፣ ለዕድገቷ ጉልበትን እንደሚያመጣላት ተስፋ የሰጠ ኾኗል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
