“በሰጥቶ መቀበል መርሕ ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሠራለን”

11
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ መድረኮች በርካታ ውስብስብ ፈተናዎችን አልፋ ሀገራዊ ጥቅሟን ያስከበሩ ጉልህ የዲፕሎማሲ ድሎችን አብስራለች። አዲስ የተመሠረተው የመደመር መንግሥትም እነዚህን ውጤቶች መሠረት በማድረግ ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ግልጽ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
👉 ባለፉት አምስት ዓመታት ከተከናወኑ ጉልህ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መካከል የብሪክስ አባልነት ማግኘት አንዱ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ባለፉት አምስት ዓመታት ከተመዘገቡ ትልልቅ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መካከል አንዱ መኾኑን አመላክቷል። ይህም የሀገሪቱን የጂኦ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
👉 የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዲፕሎማሲም ሌላው የተከናወነ ተግባር ነው። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫዎች እና የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሰነድ እንደሚያብራራው በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የተደረጉ ውስብስብ ድርድሮችን”ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚል መርሕ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር እንዲያዙ ማድረግ ተችሏል።
ከዚህ ባሻገር የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እና የውኃ ሙሌት ከተጠበቀው በላይ ተጠናቅቆ የውኃ ፍሰት ስምምነት በብዙኃኑ የተፋሰሱ ሀገራት እንዲጸድቅ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሠርቷል።
👉 የቀይ ባሕር እና የባሕር በር ዲፕሎማሲም ሌላው የተሠራ ተግባር ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ሕጋዊ፣ ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስፈላጊነትን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስገንዘብ ጉዳዩን ዓለም አቀፍ የውይይት አጀንዳ ማድረግ ችላለች።
👉 የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እና የፋኦ ሪፖርቶች ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ እና የአየር ንብረት ላይ የተሠሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መኾናቸውን ገልጸዋል። በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ችግኝ በመትከል እና በማከፋፈል የታችኛው ዓባይ ተፋሰስ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን የአየር ንብረት ለመጠበቅ የተደረገው ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አድናቆትን አትርፏል።
🎙️ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ባደረጉት ንግግር አዲሱ መንግሥት በቀጣይ ሊሠራባቸው ያሰባቸው የዲፕሎማሲ ትኩረቶችን ገልጸዋል። በዚህም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ማጎልበት አንዱ እንደኾነ ነው ያመላከቱት።
የውጭ ግንኙነታችን የኢትዮጵያን ተጽዕኖ በዓለም ላይ ሊያሳይ በሚችል መልኩ እንዲቃኝ ይደረጋል ብለዋል። ከሁሉም የዓለም አካላት ጋር ብሔራዊ ጥቅማችንን መሠረት አድርገን አብረን እንሠራለን ነው ያሉት። ጎረቤቶቻችን በተፈጥሮ ያገኘናቸው ወዳጆቻችን ናቸው፤ ከሁሉም ጎረቤቶች ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅም እና በትብብር የመሥራት መርሐችንን እንገፋበታለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊኾን አይችልም እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ግን ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሠራለን ነው ያሉት።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 🇪🇹🇪🇹
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየመደመር መንግሥት የቀጣይ አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?
Next article“የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ከጠመንጃ የበላይነት ወደ ወንድማማችነት”