
የመደመር መንግሥት ተመሥርቷል። ባለፉት ዓመታት ስኬታማ ሥራዎችን የሠራው የመደመር መንግሥት በቀጣይ ዓመታትም ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ንግግር በቀጣዮቹ ጊዜያት በሀገራዊ ምክክር ምክረ ሀሳቦች መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ይኖረናል ብለዋል።
የፖለቲካ ምሕዳሩ በትብብር እና በፉክክር ሚዛን ላይ ተመስርቶ እንዲቀጥል ይደረጋል። ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ በተለይም በምርጫ ንቁ ተሳትፎ ከነበራቸው ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት መንግሥት ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል።
የተጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሬት ረግጦ የታለመለት ግብ እንዲመታ ይደረጋል። ጠንካራ ቁጥጥር እና ክትትል ያለበት የበጀት አካሄድን እንከተላለን። ለኅብረ ብሔራዊ ሀገር መንግሥት ግንባታ ወሳኝ የኾነው የወል ትርክት ተገቢውን ትኩረት ያገኛል ብለዋል።
ምርታማነት ባሕልም ሥርዓትም እንዲኾን ይሠራል፤ የሰላም ሁኔታችንን የበለጠ ለማጽናት የውይይትን እና የይቅርታን መንገድ እንከተላለን፤ የተጠናከረ የጸጥታ እና የደኅንነት ዝግጅት፣ ክትትል እና ስምሪት ይኖረናል ነው ያሉት።
የሚዲያ ምህዳሩ ሕግን፣ ሀገራዊ እሴቶችን እና ፍላጎቶችን ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀስ ይደረጋል። ሙስናን፣ ሌብነትን፣ የዘመድ አሠራርን እና ወገንተኝነትን ለማስወገድ መንግሥት መረር ያሉ እርምጃዎችን ይወስዳል። እንደ መሶብ ያሉ ዘመናዊ አሠራሮችን እስከ ታችኛው ወረዳ በማድረስ እና የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በማጠናከር የሰርቪስ አሰጣጥ እንዲዘምን ይደረጋል ብለዋል።
የመኖሪያ ቤት ችግሮችን ከስሩ ለመፍታት አዳዲስ አካሄዶችን እንደሚከተሉም ገልጸዋል። የመንግሥት ፕሮጀክቶች ጊዜ እና ገንዘብ በሚቆጥብ ፈጠራ እና ፍጥነት እንደሚተገበሩም ገልጸዋል። የትምህርት ጥራትን የበለጠ በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ የሚገነባውን ትውልድ ለመፍጠር እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ በሞራል፣ በእሴት፣ በክህሎት እና በባለቤነት ስሜት የሚታነጽበትን መንገድ እንከተላለን ብለዋል። ኢትዮጵያ ለድርቅ፣ ለጦርነት፣ ለሉዓላዊ ኢኮኖሚ ቀውሶች፣ ለጂኦፖለቲካዊ እና ለሌሎች ማናቸውም ተግዳሮቶች የማትበገር እንድትኾን የሚያስችላትን ሁለንተናዊ የዝግጁነት ሥርዓት እንገነባለንም ነው ያሉት።
የሲቪል ሰርቪስ አሰጣጥ በሂደት ሳይኾን በውጤት እና በተጽዕኖ እንዲመዘን ይደረጋል። ባሕል እና ሥነ ጥበብ ለሀገር መንግሥት ግንባታ፣ ለሕዝቦች ትስስር እና ለኢትዮጵያ መለያ ግንባታ ተገቢውን ሚና ለመጫዎት በሚያስችላቸው መንገድ ይደገፋሉ። የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በሀገሩ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ኑሮ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
የውጭ ግንኙነታችን የኢትዮጵያን ተጽዕኖ በዓለም ላይ ሊያሳይ በሚችል መልኩ እንዲቃኝ ይደረጋል። ከሁሉም የዓለም አካላት ጋር ብሔራዊ ጥቅማችንን መሠረት አድርገን አብረን እንሠራለን፤ ከሁሉም ጎረቤቶች ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅም እና በትብብር የመሥራት መርሐችንን እንገፋበታለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊኾን አይችልምና በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሠራለን። የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የዓለም፣ የአካባቢያችንን ወቅታዊ ሁኔታ፣ የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ኃይል እንዲኖረን እንሠራለን ነው ያሉት።
በቀጣናው የአየር የበላይነት ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ ትገነባለች። የሚኖረን መከላከያ ዘመናዊ፣ በፈጠራ የታገዘ፣ ሁሌም ዝግጁ፣ ብቁ እና ንቁ፣ በየአውዶቹ የመሰማራት አቅም እና ቁመና ያለው ይኾናል ብለዋል። ችግሮች ሳይፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ማወቅ እና መግታት፣ ከመጡም መከላከል፣ ከባሰም እንደ አባቶቹ እና እንደ ልማዱ ማሸነፍ የሚችል ኀይል ኾኖ ይገነባል ነው ያሉት።
የሃይማኖት፣ የሲቪክ እና የባሕል ተቋማት ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል። የሲቪክ ተቋማት በሀገር ፍቅር መንፈስ ተቃኝተው ሲቪክ ማንነት በመገንባት ረገድ ከእስካሁኑ በላይ እንዲያበረክቱ ይደረጋል ነው ያሉት።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
