“የጠላቶቻችን ጭንቀት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እንዳትነግስ መገደብ ብቻ ኾኗል”

4
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም፤ ልማት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመደመር መንግሥት በትኩረት ሠርቷል። የስንዴ ልማትን በማስፋት ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለመላቀቅ በትኩረት ተንቀሳቅሷል።
የጋራ ተጠቃሚነትን መርሕ ባደረገው ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሕዳሴ ግድብን በስኬት በማጠናቀቅ ኢትዮጵያ በድጋሜ የአፍሪካ ተምሳሌት እንድትኾን አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ወቅት ባደረጉት ንግግር ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ኾኖ የሚኖር ታላቅ ገድል ነው ብለዋል። ጥቁሮች እንደምንችል እና እንደምናሳካ አሳይተናል ነው ያሉት።
በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ፤ በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ፍኖት ተጠናቅቆ የአፍሪካ ምልክት መኾን የቻለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሌሎች ብሥራቶችን በውኃ ማማው ሥር አፍልቆ ለኢትዮጵያውያን አጋርቷል።
የሕዳሴ ግድብ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሠራው የመደመር መንግሥት በጉባ ብሥራቶች ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት በማፍሰስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እንደሚገነባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
👉ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል የኒውክለር ማብለያ፤
👉 በአፍሪካ ግዙፍ የኾነ የአውሮፕላን ማረፊያ፤ የጋዝ ፋብሪካ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ሜጋ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ እንደሚገነቡም መናገራቸው ይታወሳል።
የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጉባ ብሥራቶች ወደ ሥራ ገብተዋል። ስኬቶችን ያስመዘገበው የመደመር መንግሥት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ የመንግሥት ምሥረታ አካሂዷል።
🌊 የአዲሱ መንግሥት ልዩ ትኩረት- ባሕር በር፤ በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ፈለግንም አልፈለግንም የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ለውጥ እኛንም ይጎበኘናል፤ ለዚህም ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል።
🌊 የባሕር በር ተጋሪነታችን የተለወጠው፣ የተጽዕኖ አድማሳችን ሲኮሰምን የኖረው ፈልገን ብቻ አይደለም፤ ተገደን ጭምር ነው። በተዘጋጀንባቸው ዘመናት ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ፣ ከሜዲትራኒያን እስከ አትላንቲክ ተጉዘናል፤ ባልተዘጋጀንበት ወቅት ደግሞ መውጫ መግቢያ በራችን ተዘግቶብን ነበር ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ጉዳይ ላይ የምትወስን መኾኗን በሰዎች ችሮታ ሳይኾን በጉልበቷ ታረጋግጣለች ብለዋል። የጠላቶቻችን ጭንቀት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እንዳትነግስ መገደብ ብቻ ኾኗል ነው ያሉት።
ከሁሉም የዓለም አካላት ጋር ብሔራዊ ጥቅማችንን መሠረት አድርገን አብረን እንሠራለን ብለዋል። የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊኾን አይችልም እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ወጥታ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሠራለን ነው ያሉት።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በጋራ ተጠቃሚነት እና በዲፕሎማሲያዊ አግባብ አስተማማኝ የባሕር በር ይኖረን ዘንድ ያደረግነው ጥረት ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እና ይሁንታ እንዲያገኝ መሠረት ጥሏል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በጋራ የማደግ እና የመበልጸግ የመሻት በጎ ሃሳቧን ያሳየ እንደኾነ ነው የገለጹት።
አስተማማኝ የባሕር በር መሻታችን በጋራ ጥቅም ሰጥቶ በመቀበል እና በሰላማዊ መንገድ እውን እንዲኾን ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 🇪🇹🇪🇹
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያውያን ሕልውና አንድም ከቀይ ባሕር፤ ሁለትም ከዓባይ ሸለቆዎች ጋር የተሳሰረ ነው።
Next articleየመደመር መንግሥት የቀጣይ አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?