የኢትዮጵያውያን ሕልውና አንድም ከቀይ ባሕር፤ ሁለትም ከዓባይ ሸለቆዎች ጋር የተሳሰረ ነው።

6
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ከ1ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚዘልቅ ሰፊ የባሕር ክልል ባለቤት እንደነበረች የታሪክ መዛግብት ምስክሮች ናቸው።
ከጥንቷ አዶሊስ እስከ አሰብ እና ምጽዋ ያሉ ስትራቴጂያዊ ወደቦቿን በበላይነት እና በባለቤትነት ለዘመናት ስታስተዳድርም ኾነ ስትገለገልባቸው ኖራለች።
በእርግጥም ቀይ ባሕር በኢትዮጵያ የታሪክ ገጽ ላይ ባለብዙ መልክ እና ጥልቅ ትርጉም ያለው የታላቅነቷ ማሕተም ነው። ይህ የውኃ ሃብት ለሀገሪቱ ጥንታዊ ሥልጣኔ መነሻ እና መዳረሻ ከመኾኑም በላይ የተፈጥሮ ወሰኗ ኾኖ ያገለግል ስለነበር ያለፉት ዘመናት ነገሥታት በሉዓላዊነት እና በበላይነት አሥተዳድረውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሰሞኑን እንደገለጹት “አቅም በነበረን ወቅት የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን ወስነናል፤ በተዳከመን ጊዜ ግን ሌሎች በእኛ ላይ ወስነውብናል፤ በተዘጋጀንባቸው ዘመናት ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ፣ ከሜዲተራኒያን እስከ አትላንቲክ ተጉዘናል፤ ባልተዘጋጀንበት ወቅት ደግሞ መውጫ መግቢያ በራችን ተዘግቶብናል” ብለዋል።
በእርግጥም የኢትዮጵያውያን ህልውና የተገነባው እና ታሪካቸው የተቀዳው ከቀይ ባህር እና ከዓባይ ሸለቆዎች መኾኑ አይካድም። የዘርፉ ምሁራንም እንደሚያስረዱት የኢትዮጵያ ህልውና እና የሥልጣኔ ታሪክ ከእነዚህ ሁለት ስትራቴጂያዊ የውኃ ሃብቶች ተነጥሎ ሊታይ አይችልም።
ኾኖም ሀገሪቱ ወሳኝ ስትራቴጂያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የነበረውን የአሰብ ወደብ በታሪክ አጋጣሚ ካጣችበት ጊዜ ጀምሮ ለሦሥት አሥርት ዓመታት ያህል የተሻገረ ብሔራዊ የህልውና አደጋ ተጋርጦባታል።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ይህን በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን እና የተፈጥሮ መብቷ የኾነውን የባሕር በር ዳግም ለማግኘት ፍላጎቷን ብሔራዊ አጀንዳ አድርጋ ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ገብታለች።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሰላማዊ መንገድ አስተማማኝ የባሕር በር እንዲኖራት የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ሀገሪቱ በዲፕሎማሲያዊ አግባብ የባሕር በር ለማግኘት ያደረገችው ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እና ይሁንታ ለማግኘት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት መጣሉንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በቀይ ባሕር እና በህንድ ውቅያኖስ መገናኛ እንዲሁም በዓለም የነዳጅ መስመር አቅራቢያ መገኘታቸው ልዩ ዕድልም ፈተናም መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አብራርተዋል።
አቅም ገንብተን ጠንክረን ከተገኘን የራሳችንን ዕድል ራሳችን እንደምንወስን፣ ከተዳከምን ግን ሌሎች እንደሚወስኑብን አሳስበዋል። ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅም እና በትብብር የመሥራት መርህን አጽንታ ትቀጥላለች፤ የሀገሪቱ ሥልጣኔ እና የኢኮኖሚ ዕድገት ያለ ባሕር በር ሙሉ ሊኾን ስለማይችል፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመስርታ የባሕር በር እንዲኖራት በትኩረት እንደሚሠራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የነፍጥ አዙሪትን በዘላቂነት ማስቀረት ይገባል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ