“የነፍጥ አዙሪትን በዘላቂነት ማስቀረት ይገባል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

7
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ሥብሠባቸውን አካሂደዋል። በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ሥብሠባ የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም ኢትዮጵያ በማይናወጥ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንድትጸና፣ ዜጎቿም ለሀገር ብልጽግና ያላቸው ርዕይ፣ የጋለ መሻት እና የነገውን ትውልድ ባሰበ የአገልጋይነት መንፈስ የሚተጉ እንዲኾኑ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
የሀሳብ ጥልቀት፣ የዕውቀት ደርዝ፣ የሥነ ምግባር ከፍታ፣ የእሳቤ ባለቤት እና የመከወን ተነሳሽነት አንጡራ ሃብቶቻችን የኃይል ምንጮቻችን ይኾናሉ ብለዋል።
የሀገራችንን የተለምዶ የፖለቲካ ማጠንጠኛ ውርስ ከኾነው ከአምባጓሮ አመጽ እና የግጭት ጎዳና መላቀቅ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። “የጠመንጃ ባሕልን እና የነፍጥ አዙሪትን በዘላቂነት ማስቀረት ይገባል” ብለዋል።
የፖለቲካ ልምምዳችን በሰላም፣ በንግግር፣ በዕውቀት እና በመደማመጥ ላይ እንዲመሠረት መንግሥት ከፍ ያለ ትኩረት ይሰጣል ነው ያሉት። ለዚህም በሀገራዊ ምክክር ሂደት በውይይት የዳበሩ ሀገራዊ ሀሳቦች ወደ መሬት እንዲወርዱ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ሙስናን እና ሌብነትን አምርሮ የሚታገል ማኅበረሰብ ለመፍጠር መንግሥት የጀመራቸው እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
ለኢትዮጵያን የሚመጥናት ሰላም፣ እድገት፣ ብልጽግና እና አንድነት በመኾኑ ሴራን እና ግጭትን የሚጠነስሱ የአዕምሮ እና የሀሳብ ውቅሮችን መንግሥት አምርሮ ይታገላል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያዊነት እሳቤ በእያንዳንዱ ጋሬጣ የሚደናቀፍ አይደለም ብለዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንጊዜም ከእውነት እና ከታሪክ ጋር የሚሰለፍ አስተዋይ ሕዝብ ነው ብለዋል። መንግሥትም ይህንን ዕሴት አክብሮ እንደሚያስከብር አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleጥናቶቹ ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለተመራማሪዎች ግብዓት ኾነው ያገለግላሉ።