
የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት 5ኛውን ዙር የሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት በአማራ ክልል ደረጃ ይፋ ማድረጊያ መድረክ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ሀብታሙ ጤናው ተቋሙ መረጃዎችን በቆጠራ ወይም በናሙና ጥናቶች ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ በመሠብሠብ፣ በመተንተን እና በማቀናበር ለተጠቃሚዎች እንደሚያሰራጭ ተናግረዋል።
አገልግሎቱ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ጥናቶችን እንደሚያከናውንም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ልማት ዕቅድ የታቀዱት የግብርና ናሙና ቆጠራ፣ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ፣ የሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት፣ የብሔራዊ የተቀናጀ ቤተሰብ ጥናትን በዋናነት ጠቅሰዋል።
የእነዚህ ጥናቶች የመረጃ መሠብሠብ ሥራ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል። የሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት ስታቲስቲካዊ መረጃ ለተጠቃሚዎች ሙሉ በሙሉ መሰራጨቱንም አስታውቀዋል።
ከእነዚህ መካከል የብሔራዊ የተቀናጀ ቤተሰብ ጥናት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፣ የፍልሰት እና የሥራ ስምሪት ስታቲስቲክስ ዋና ዋና አመላካቾች ባለፈው ይፋ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
የግብርና ናሙና ቆጠራ እና የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ውጤቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል። ጥናቱ ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ በናሙና ከተመረጡ ቤተሰቦች የተሠበሠበ እና በርካታ ክልላዊ አመላካች መረጃዎችን የያዘ እንደኾነም አስታውቀዋል።
ጥናቱ የውልደት መጠንን፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀምን፣ የእናቶች ጤናን፣ የልጆች እና የእናቶች አመጋገብ ሁኔታን፣ የሕጻናት ክትባትን፣ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ግንዛቤ እና መከላከልን የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ስታቲስቲካዊ መረጃዎች አጠቃልሎ የያዘ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የተሠበሠቡት መረጃዎች ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለተመራማሪዎች ግብዓት ኾነው እንደሚያገለግሉም ተገልጿል። የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር) የተሠበሠቡት መረጃዎች የ25 ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ ለመከለስ፣ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ለማዘጋጀት፣ የዘላቂ ልማት ግቦችን እና የሰው ልጅ ዕድገት አመልካችን በትክክል ለመለካት ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አላቸው ነው ያሉት።
የመንግሥት አሥፈጻሚ አካላት እነዚህን መረጃዎች ለውሳኔ አሰጣጥ እና ለሕዝብ አገልግሎት በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
