በጥልቅ ሃሳብ መመራት እና ችግሮችን አስቀድሞ መለየት የኢትዮጵያ ብሩህ መንገድ አመላካቾች ናቸው።

5
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ሥብሠባ ተካሂዷል። በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ሥብሠባ የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መንግሥት የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ ሁሉንም
የጥንካሬ አቅሞች በማደራጀት የኢትዮጵያን ዕድገት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ላቅ ያሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ልምምድ ለማዘመን መንግሥት እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጅ መቀረጹ፣ የሀገርን ጥቅም ለማስከበር አያሌ ወዳጆችን ማበራከት መቻሉ፤ የደኅንነት እና የጸጥታ ዘርፎች ይበልጥ እንዲዘምኑ መደረጉ፤ የትምህርት እና የጤና፣ የከተማ እና የገጠር ልማቶች ከኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅሞች ጋር እንዲተሳሰሩ ጉልህ የኾኑ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች የሚከበሩት በቀዳሚ ረድፍ ላይ የተቀመጡ ግቦችን በርትቶ በመተግበር ላይ ብቻ አይደለም፤ እልፍ ብሎ በማሰብ ላቅ ሲልም ጊዜን እና ዘመንን የሚቃኙ ደፈር ያሉ ስትራቴጂያዊ እሳቤዎችን ነድፎ ሀገርን ከፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ሃሳብ በመያዝም ጭምር ነው ብለዋል።
በቅርቡ የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር ማኅበራዊ እሴቶችን በማስተሳሰር፤ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በጽኑ የሃሳብ አምድ ላይ በማነጽ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሃሳብ ልእልና የሚያምን ለሕዝብ የተገዛ፣ ስክነት የጋራ ሃብቱ እንዲኾን ያስቻለ ክዋኔ ነው ብለውታል።
ኅብረተሰቡ የተቀላጠፈ እና ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የተወሰዱ የዲጂታላይዜሽን እርምጃዎች እና የሥራ ሂደትን የማሳለጥ በጎ ጅምሮችንም አበረታተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ተቀዳሚ ትኩረታቸው ሰላም እና ብልጽግና መኾኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ በተቃራኒ ከቆሙ አካላት ጋር ለመነጋገር እና ለመወያየት የታየውን ዝግጁነት እና ውጤታማ ሂደት በአብነት አንስተዋል።
በሌላም በኩል በጋራ ተጠቃሚነት እና በዲፕሎማሲያዊ አግባብ አስተማማኝ የባሕር በር ይኖረ ዘንድ ያደረግነው ጥረት ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እና ይሁንታን እንዲያገኝ መሠረት ጥሏል ነው ያሉት። የኢትዮጵያን በጋራ የማደግ እና የመበልጸግ በጎ ሃሳቧን ያሳየ ነውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ አንድነት እና ሕልውና ላይ ያነጣጠሩ ውስጣዊ እና አካባቢያዊ የባላንጣነት ሃሳቦችን እና ፍላጎቶችን አስቀድሞ በመለየት በቂ ዝግጅት በማድረግ፤ የነገን እና የወደፊት ፈተናዎችን በመመልከት ሁለንተናዊ አቅምን ማዳበር እና የመፈጸም ክህሎትን ማላቅ ተገቢ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የመፈጸም አቅምን ማጠናከራችን ሳይታሰቡ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል ሥርዓት ማበጀታችን እንደ ሀገር ፍቱን አካሄድ ነው ብለዋል። አሁን ካለው ተሞክሯችን ዐይተን በጋራ ለመመስከር ችለናል ነው ያሉት።
በጥልቅ ሃሳብ መመራት፤ ችግሮችን አስቀድሞ መለየት፤ ፍቱን እና ተሻጋሪ መፍትሔ ማዘጋጀት የኢትዮጵያን ብሩህ መንገድ የሚያመላክቱ መኾናቸውን ፕሬዝዳንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሐዝ እንዲወርድ በትኩረት ይሠራል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
Next articleጥናቶቹ ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለተመራማሪዎች ግብዓት ኾነው ያገለግላሉ።