‎የ2019 ዓመት ዕቅድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስከብር ነው።

3
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ሥብሠባ ተካሂዷል። በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ሥብሠባ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ንግግር አድርገዋል።
በዚህም የተያዘውን የ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫን አብራርተዋል። የትኩረት አቅጣጫው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞችን ይበልጥ የሚያስከብር እና ፈጣን ዕድገቷን የሚያረጋግጥ መኾኑን ገልጸዋል።
ዕቅዱን እውን ለማድረግም አዳዲስ አሠራሮችን እና አደረጃጀቶችን መከተል ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ እንደኾነ ነው ያመላከቱት።
የ2019 ዕቅድን ለመፈጸም የሚመደቡ አካላት የሕዝብን ፍላጎት ያስቀደሙ፣ የዛሬን እና የወደፊት ራዕያችንን ጭምር የሚመለከቱ፣ ጊዜን እንደ አንጡራ ሀብት የወሰዱ እና ፋይዳውንም ከፍ አድርገው የሚረዱ፣ የዋዛ ፈዛዛ ልምምድን የሚጠየፉ እና ትጋት ያላቸው ሀገራዊ አገልጋዮች እንዲኾኑ ይጠበቃል ብለዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ የበጀት ዓመቱ ዋና ትኩረቶች፦
👉ሰላም ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ግስጋሴ ያለውን ዋጋ ያጤነ እና ከመቸውም ጊዜ የበለጠ ኅብረትን፣ ትብብርን እና ኢትዮጵያን የሚያስቀድም ተግባር ኾኖ የሚከናወን ይኾናል።
👉ጥራትን መሠረት ያደረገ ሁለንተናዊ እና መዋቅራዊ ሽግግር እንዲኖር ይደረጋል።
👉የፕሮጀክት እና የፕሮጀክት ፋይናንስ አፈጻጸም ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ተጠያቂነት ያለው እንዲኾን ይሠራል።
👉የታክስ መሠረትን በማዘመን እዳን በሚገባ መልኩ ማሥተዳደር እንዲሁም የመንግሥት ወጭ እና ገቢን በአግባቡ የመቆጣጠር አቅም ያድጋል።
👉በፌዴራል እና በክልሎች መካከል ያለው የሥራ ቅንጅት እና አፈጻጸም የተባበረ፣ የተደጋገፈ፣ ቀልጣፋ እና እንከን አልባ እንዲኾን ይደረጋል።
👉የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ከተቀባይነት ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያሻግር በተለይም ወዳጆችን በማበረታታት የሚተጋ የደመኝነት ዕይታ
ያላቸውን ደግሞ የሚመክር፣ ለቀጣናዊ ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ምንጊዜም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ተነሳሽነቶች ያሉት እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነታችን የሚያሳድግ ይኾናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የሀገር ውስጥ ገቢ 1 ትሪሊዮን 980 ቢሊዮን ብር ደርሷል” የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
Next article“የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሐዝ እንዲወርድ በትኩረት ይሠራል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ