‎የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መታወቂያ፦የጋራ ዕድገት እና ተጠቃሚነት ላይ የጸናው ዲፕሎማሲ።

2
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ ጎልታ የምትታወቅበት የዲፕሎማሲ አሻራ በትውልዶች መካከል የተሻገረ ጽኑ አለት ነው። አህጉሪቱ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር በነበረችበት የፈተና ዘመን ኢትዮጵያ “የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን” የሚል ታላቅ መርህ በመንደፍ የፓን-አፍሪካዊነት ፋና ወጊ ኾናለች።
ይህ አካሄድ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) በአዲስ አበባ ከተማ እንዲመሠረት ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ኾኖ ያገለገለ ሲኾን ዛሬም ድረስ የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት መሪ ኮምፓስ ነው።
ዓለም በጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻ እና በጎራ መከፋፈል እየታመሰች ባለችበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከታሪካዊ መሠረቷ የተቀዳውን እና ዘመኑን የዋጀውን “የጋራ ተጠቃሚነት” የዲፕሎማሲ አካሄድ ይዛ ቀጥላለች። ይህ ስትራቴጂዋ ከዓለም ኀያላን እስከ ታዳጊ ሀገራት በትኩረት የምትታይ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትኾን አድርጓታል።
ይህ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባልነቷ ጀምሮ የነበረ የጥንካሬዋ ማሳያ ነው። አሁን ላይ ሌሎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በአባልነት ለመቀላቀል ለምታደርገው ጥረት የጎላ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት እየፈጠረላት እንደሚገኝ ተገልጿል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት እንደመኾኗ የቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች አሸማጋይ ናት።
“የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን” በሚለው ዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂ የራሷን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞች እያስከበረች ለአህጉራዊ ትስስር መጠናከር የእናትነት ሚናዋን እየተወጣች ቀጥላለች።
በዚህ ስትራቴጅዋ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የነበሩ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን እና ፖለቲካዊ ውጥረቶችን ወደ አፍሪካ ኅብረት መድረክ ማምጣት ችላለች። በዚህም የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን እና ኢ-ፍትሐዊ የኾኑ ወሳኔዎችን በር ዘግታለች።
በተጨማሪም በሌሎች አማራጭ መድረኮች ስትሳተፍ የአፍሪካውያንን የጋራ አጀንዳ በማንጸባረቅ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና የፖለቲካ ክንውኖች ላይ ተገቢውን የውሳኔ ሰጭነት ቦታ እንድታገኝ በጽኑ ድምጿን እያስተጋባች ትገኛለች።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article‎ለሀገር አና ለሕዝብ ደኅንነት በቁርጠኝነት እንሠራለን።
Next article‎”የመረጣችሁ ሕዝብ ከእምነት ጋር ታላቅ አደራ ጥሎባችኋል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ