‎ለሀገር አና ለሕዝብ ደኅንነት በቁርጠኝነት እንሠራለን።

2
‎በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል “ሀገር እንገነባለን እንጅ ሀገር አናፈርስም” በሚል መሪ መልዕክት ሥልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የሰላም ኀይሎች ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ተመርቀዋል።
‎
‎በመርሐግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ለማስመለስ የትጥቅ ትግል በመተው የሰላምን አማራጭ መከተል ተገቢ መኾኑን ተናግረዋል። ‎ሥልጠናውን የወሰዱ የሰላም ኀይሎች ከመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት ሰላምን ማስከበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
እናንተ የሰላም ወዳዱ ሕዝብ ልጆች ናችሁ ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አንተነህ ታደሰ የሰላም ኀይል አደረጃጀት የሕዝብ አገልጋይ በመኾን ከሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ጋር የሕዝቡን ሰላም ማረጋገጥ ይኖርባችኋል ብለዋል።
‎
‎ያለችን ሀገር አንዲት ናትና ክብሯን እና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የጋራ ኀላፊነታችን መወጣት አለብን ነው ያሉት። ‎‎የሰላም ኀይል የጎንደር ቀጣና ሠብሣቢ መልካሙ ጣሴ ሥልጠናው ወቅቱን በመረዳት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያለመ ነው ብለዋል። የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ከትጥቅ ትግል መውጣት ይገባል ነው ያሉት።
‎
ባልተገባ መንገድ ሕዝቡን ላልተገባ ስቃይ እና በደል ዳርገናል ያሉት ሠልጣኞች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ በመከተል የበደልነውን ማኅበረሰብ ለመካስ እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንሠራለን ብለዋል። ‎ባገኙት አዲስ ዕውቀት እና ልምድ ለሀገር አና ለሕዝብ ደኅንነት በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም አንስተዋል።
‎
‎በቀጣይም መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።
‎
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አደራጀው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ጠንካራ ሥርዓት መገንባት ጥበብ እና ስክነትን አጣምሮ የያዘ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article‎የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መታወቂያ፦የጋራ ዕድገት እና ተጠቃሚነት ላይ የጸናው ዲፕሎማሲ።