
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤት መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ሥብሠባ እየተካሄደ ነው። ምክር ቤቱ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)ን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በምክር ቤቱ ባስተላለፉት መልእክት የ2010 ዓ.ም ለውጥን ያመጣው በአዲስ ትውልድ ውስጥ ያለው ዓለምን አሸንፎ የመጓዝ ፍላጎት ነበር ብለዋል።
ለብዙ ተደጋጋሚ ጊዜያት የኢትዮጵያ ለውጦች የሚገፋቸው ቁጭት እንደነበርና ሀገር ወደኋላ ስትቀር እና ዓለም ወደፊት ሲራመድ የሚፈጠር ቁጭት እንደኾነም ጠቁመዋል። “ይነዳል ይቆጫል እንደ እግር እሳት፤ ወደፊት ሲሄዱ ከኋላ መቅረት” የተባለውም በምክንያት ነበር ነው ያሉት።
ይህንን ቁጭት በተገቢው ሥርዓት የማስተናገድ ፈተና መኖሩ ከባዱ ነገር እንደነበርም አንስተዋል። ቁጭት መነሻ እንጅ ማድረሻም መዳረሻም አይኾንም ብለዋል። ማድረሻው ሥርዓት ሲኾን መዳረሻው ደግሞ ሥልጣኔ እንደኾነ ነው የጠቆሙት።
ቁጭት ሥርዓትን እንዲወልድ ሰክኖ ማሰብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ማሰብ፣ ማንሰላሰል፣ መመርመር፣ መሞከር፣ የተሻለውን መምረጥ እና ማሻሻል ሥርዓትን የሚገነቡ ቅመሞች መኾናቸውንም ገልጸዋል። ምክንያቱም ሥርዓት በአንድ ጀንበር ተገንብቶ ስለማያልቅ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ሥርዓት በሂደት የሚፈጠር፤ ትዕግሥት እና ትጋትን እኩል የሚጠይቅ፤ ጥበብ እና ስክነትን አጣምሮ የያዘ መኾኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሥርዓትን የመገንባት ሙከራዎች የቁጭት ችግር እንዳልነበረባቸው አውሰተዋል። በአንጻሩ የእፎይታ እና የስክነት ችግር እንደነበረባቸው ነው ያነሱት። ለአዲስ ሃሳብ ዝግ የመኾን ጸባይም ይታያል ነው ያሉት።
ነባራዊ ሁኔታውን ተገንዝቦ ለኢትዮጵያ የሚኾነውን አዋጭ መንገድ መርጦ መንገዱን ፈትኖ እና አረጋግጦ ኢትዮጵያዊ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል እፎይታ እና ዝግጁነት ያንሳል፤ በዚህ ምክንያት የወቅቱ መሪዎች ለኢትዮጵያ ከሚያዋጣው ይልቅ አቋራጩን ሲመርጡ ኖረዋል ነው ያሉት።
ምንጩን የሚረሳ ወንዝ ያለጥርጥር ይደርቃል እንደሚባል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስሩ የተነጠለ ሕዝብም መጨረሻው አያምርም ብለዋል። ዓላማውን እና ጥንካሬውን ያጣል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
