
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመኾን በምክር ቤቱ ተሹመዋል። ለምክር ቤት አባላትም ንግግር እያደረጉ ነው።
ዓለም የመጀመሪያዎቹን የኢንዱስትሪ አብዮቶች ስታካሂድ ሀገራችን በውስጣዊ የዘመነ መሳፍንት ሽኩቻ ተጠምዳ በመቆየቷ ከአብዮቶቹ ተጠቃሚ ሳትኾን መቅረቷን አስታውሰዋል። የእርስ በርስ ግጭትም አቅማችንን በማዳከሙ የውጭ ወራሪዎች ሲመጡ ጉልበታችን የተመናመነ እንዲኾን አድርጎታል።
በዓድዋ ጦርነት አንገቱን ደፍቶ የተመለሰው ጠላት ለዓመታት ራሱን ሲያዘጋጅ ሀገራችን ግን በድሉ ማግስት አሸልባ ቆይታለች።
በዚህም በማይጨው ጦርነት ጠላት ዘመናዊ የሁለተኛው ኢንዱስትሪ አብዮት ውጤት በኾኑ አውሮፕላኖች በሰማይ ሲመጡ ያልተዘጋጀንበትን ፈተና ለመጋፈጥ ተገድደናል። “በአንድ እንቅፋት አንዴ መመታት ተፈጥሯዊ ቢኾንም ደጋግሞ መመታት ግን የጤና አይደለም” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ቀንድ፣ የቀይ ባሕር፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና አጠቃላይ የዓለም ጂኦፖለቲካ በፍጥነት እየተለዋወጠ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ምሥራቅ አፍሪካ፣ ቀይ ባሕር እና የሕንድ ውቅያኖስ በሚገናኙበት ወሳኝ ስፍራ ላይ በመኾኗ ይህ የለውጥ ማዕበል ፈለግንም አልፈለግንም ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የዝናብ ጠብታ ጣሪያ አይቶ እንደማያልፍ ሁሉ በታሪክም የኃያላን ሽኩቻ በቀጣናችን ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ሀገራችንን ለጦርነት እና ለባሕር በር መዘጋት ዳርጓታል ብለዋል።
አቅም በነበረን ጊዜ የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን ስንወስን በተዳከምንበት ወቅት ደግሞ ሌሎች በእኛ ላይ ወስነዋል ነው ያሉት።
አሁንም ዓለም አዲስ ቅርጽ እና መልክ እየያዘች ባለችበት በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ አሸናፊ የሚኾኑት ቶሎ የነቁ እና አቅማቸውን የገነቡ ብቻ መኾናቸውን አስምረውበታል። በመኾኑም የውስጥ እንከን መፈለግን ትተን ለሚመጣው ዓለም አቀፍ የለውጥ ማዕበል ሳንሸበር እና ሳንበረግግ ሀገራችንን ለማሻገር ራሳችንን በብቃት ማዘጋጀት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
