
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል።
ምክር ቤቱ በጉባኤው የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርን እና ሌሎችንም ሹመቶችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒነት ባለው መልኩ መጠናቀቁ ይታወሳል። በምርጫው 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 10 ሺህ 438 እጩዎች እና ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች ተሳትፈዋል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።
ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ እንደኾነ ይደነግጋል፡፡ የምክር ቤቱም የሥራ ዘመን መስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እንደሚጀመር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 ተደንግጓል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል ያደራጃል ወይም ያደራጃሉ። ይመራል ወይም ይመራሉ ተብሎ ተደንግጓል፡፡
በዚህም መሠረት ዛሬ መስከረም 25/2019 ዓ.ም የመንግሥት ምሥረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት መከናወን ጀምሯል፡፡
በሕዝብ የተመረጠው መንግሥት ቀጣዩን አምስት ዓመታት ሀገር እና ሕዝብ የመምራት ኀላፊነት ዛሬ ይረከባል፡፡
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በአብላጫ ድምጽ ማሸነፉ ይታወሳል። አብላጫ ድምጽ ያገኘው ፓርቲም ለቀጣይ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን ይመራል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
