የኢትዮጵያ ቀጣናዊ የሰላም ዲፕሎማሲ አቅም እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት !

3
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ መንግሥታቸው የተከተለው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፖሊሲ በቀጣናው እና በሀገር ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ ምህዳር የቀየረ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
ለበርካታ ዓመታት በውጥረት፣ በግጭት እና በጥርጣሬ የተሞላውን የቀጣናውን ፖለቲካ ወደ አንድነት እና ትብብር ለመቀየር ጥረት የተደረገበት፣ ታሪካዊ ውጤቶች የተመዘገበበት ወቅትም ነበር። የተወሰዱት የዲፕሎማሲ እርምጃዎች የኢትዮጵያን የሰላም እና የልማት ቁርጠኝነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተግባር ያሳየ ነው።
ለአብነትም ለበርካታ ዓመታት በውጥረት የቆዩትን ኢትዮጵያን እና ኤርትራን ዳግም የማቀራረብ እርምጃ የሚጠቀስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአስመራ ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን እና ውይይቶችን በማድረግ የሁለቱን ሀገራት የቀደመ አንድነት እና ወንድማማችነት ለማጠናከር ጥረት አድርገዋል። ይህ የሰላም ጥረት ለአፍሪካ ቀንድ አዲስ የትብብር ተስፋ የሰጠ ነበር። ይህ የሰላም ጥረት በኤርትራ እስኪገፋ ድረስ ተጠናክሮ የቀጠለም ነበር።
​በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት የተፈጠረውን ውጥረት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዷቸው እርምጃዎች ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ ለጋራ ተጠቃሚነት እና ለሰላማዊ ውይይት ያላትን ዝግጁነት ያስመሰከረ ነበር።
በተመሳሳይ ከጎረቤት ሀገራት ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲ እና ኬንያ ጋር በተደጋጋሚ ሁለተናዊ እና ቀጣናዊ ውይይቶችን አድርገዋል።
እነዚህ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር እና የጸጥታ ሥጋቶችን በጋራ ለመፍታት ያለሙ፣ ተባብሮ ማደገን መሠረት ያደረጉ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ናቸው።
​በሀገር ውስጥ በኩል የተወሰዱት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችም ሰላማዊ የፖለቲካ ባሕልን ለመገንባት መሠረት የጣሉ ናቸው። በውጭ ሀገራት ተሰድደው በትግል ላይ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና መሪዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል። በሀገራቸው በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በመንግሥት በኩል ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ ድርጅቶችን ከዝርዝር ማውጣት፣ የይቅርታ አዋጅ ማወጅ እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ውስጥ ማካተት ችለዋል። ይህ እርምጃ ለዓመታት የቆየውን የጠላትነት ፖለቲካ በማስቀረት አዲስ የአካታችነት እና የውይይት ባሕል እንዲመጣ አዲስ ባሕል አምጥቷል።
በእነዚህ እና በሌሎችም ቁርጠኝነት የተሞላባቸው ውሳኔዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ዓለም አቀፍ ዕውቅና አስገኝቶላቸዋል።
በቅርቡ ደግሞ ለዘመናት መሠረታዊ የኾኑ ችግሮችን በመለየት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ ተችሏል። ለዚህ ስኬታማ ጉባኤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሚመራው መንግሥት የወሰደው እርምጃ ቀዳሚ ነበር።
በቀጣናው እና በሀገር ውስጥ የተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም፣ ለቀጣናዊ ትስስር፣ ለጋራ ልማት እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳዩ ናቸው።
የውጭ ዲፕሎማሲውን ከግጭት ወደ ትብብር፣ የሀገር ውስጥ ፖለቲካውን ደግሞ ከአግላይነት ወደ አካታችነት ለመቀየር የተደረገው ጥረት ሀገሪቱ በቀጣናው የምትጫወተውን አወንታዊ ሚና የበለጠ ያጎላው ነው። ኢትዮጵያ በቀጣናው ውስጥ የሚኖራትን የመሪነት ሚናም በግልጽ ያሳየም ነው።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
🇪🇹
በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article‎ከውጭ ጥገኝነት ወደ ሀገር በቀል የምርት ሉዓላዊነት
Next article‎የፌዴራል መንግሥት ምስረታ ዛሬ ይካሄዳል።