‎ከውጭ ጥገኝነት ወደ ሀገር በቀል የምርት ሉዓላዊነት

0
‎‎ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነቷን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ የማኑፋክቸሪንግ እና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ድጋፍ በማድረግ ፈጣን የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጋለች።
‎ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደቱ ሁሉንም ሀገራዊ ሃብቶች አቀናጅቶ በመጠቀም ላይ የተመሠረተ ሲኾን ኢንዱስትሪ ደግሞ የዚሁ ዘመናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዋና ሞተር ኾኖ እያገለገለ ይገኛል።
‎
‎የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ.ር) የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ሚና በአንድ ወቅት ሲያስረዱ ለሌሎች የልማት ዘርፎች የጀርባ አጥንት በመኾን የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት እያነቃቃ የሚገኝ መኾኑን ነው ያብራሩት።
‎
‎በተለይም በግብርናው ዘርፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን በማምረት፣ ለቱሪዝም ዘርፉ ደግሞ አስፈላጊ የመሠረተ ልማት ግብዓቶችን በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
‎
‎በ2014 ዓ.ም የተጀመረው ሀገራዊ የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በተለያዩ ምክንያቶች ተስፋ ቆርጠው እና ሥራ አቁመው የነበሩ በርካታ ፋብሪካዎች ዳግም ወደ ምርት እንዲመለሱ አድርጓል።
‎
‎የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እነዚህ ፋብሪካዎች በተደረገላቸው አጠቃላይ ድጋፍ ወደ ሥራ የተመለሱ ሲኾን ፋብሪካዎች አበረታች ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል። በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ አረጋግጠዋል።
‎
‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአንድ ሀገር እውነተኛ ሉዓላዊነት እና ነፃነት የሚረጋገጠው በራሱ አቅም አስፈላጊ የኾኑ ምርቶችን ማምረት ሲችል ነው ማለታቸው ይታወሳል።
‎
‎በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በገበያ ውስጥ ያላቸው ድርሻ እያደገ ሲመጣም ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬያን ለማዳን፣ ሀገራዊ ክብርን ለመጠበቅ እና የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
‎
‎በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬ አሥተዳደር መሻሻል እና ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር በመፈጠሩ እንደ ሴራሚክ፣ ብረት፣ መስተዋት፣ ሲመንቶ እና ወርቅ ያሉ የሀገር ውስጥ የማዕድን ሀብቶችን የሚጠቀሙ ግዙፍ ፋብሪካዎች በስፋት ወደ ሥራ እየገቡ ይገኛሉ።
‎
‎በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ግልጽ በኾነ ፖሊሲ የሚመራ ሲኾን በአርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ (ኤአይ) እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዙ ፋብሪካዎች እየተስፋፉ ነው። ከውጭ ይገቡ የነበሩ ከ96 በላይ የኢንዱስትሪ ምርቶች ተለይተው በሀገር ውስጥ ተክቶ ለማምረት ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገም ይገኛል።
‎
‎
‎
‎
‎ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleባለፉት አምስት ዓመታት በሌማት ትሩፋት ምን መሠረታዊ ለውጥ መጣ?
Next articleየኢትዮጵያ ቀጣናዊ የሰላም ዲፕሎማሲ አቅም እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት !