ቴክኖሎጂ ያረቀቀው ሉዓላዊነት:- የኢትዮጵያ የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት የላቀ ሽግግር።

3
 
ኢትዮጵያ ወደ ዕድገት ጎዳና ስታመራ እና ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ስትገነባ የሚነሱባትን ስጋቶች ቀድሞ መመከት የሚያስችል አስተማማኝ ዋስትና ያስፈልጋታል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታትም የሀገርን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ፣ ገለልተኛ እና በቴክኖሎጂ የላቀ የጸጥታ እና የደኅንነት ተቋማዊ መዋቅር መገንባት ችላለች።
ታሪካዊ ነው የኾነው ይህ የለውጥ ሥራም የተቋማቱን ስብራት ከመጠገን ባለፈ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በማላቀቅ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም ብቻ እንዲቆሙ አድርጓል።
አካሄዱ በሰው ኀይል ብዛት ላይ ብቻ ከተንጠለጠለ አሠራር በመውጣት የጸጥታ ተቋማቱን በመረጃ ትንተና፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በዘመናዊ የክትትል ቴክኖሎጂዎች ማስታጠቅ ላይ ያተኮረ ነው።
በዚህም መሠረት የሀገሪቱ የአየር ኀይል፣ የድሮን ቴክኖሎጂ፣ የዘመናዊ ፖሊስ ዕዝ መቆጣጠሪያ ማዕከላት እና የዲጂታል ፎረንሲክ አቅሞች አስገራሚ በኾነ ፍጥነት አድገዋል።
በተለይም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር ተናቦ እንዲሠራ መደረጉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ ለማክሸፍ እና ወንጀልን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል አቅም ፈጥሯል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የሀገር ውስጥ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን በማዘመን ራሱን በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች እና ራዳሮች በመገንባት የትጥቅ ጥገኝነትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ችሏል።
የተቋማቱን ሁለንተናዊ ዝግጁነት እና መዋቅራዊ ሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሲገልጹት “የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የሕዝቧን ሰላም የሚያስጠብቀው በዘመናዊ ዕውቀት የተካነ እና በቴክኖሎጂ ልዕልና የታጠቀ የጸጥታ ኀይል ሲኖር ነው” ብለዋል።
“ዛሬ በራሳችን መከላከያ ኢንዱስትሪዎች ዘመናዊ መሣሪያዎችን ማምረት ችለናል፤ ይህ የገነባነው መዋቅር ለጠላት የሚያስፈራ፣ ለዜጎች ደግሞ ከለላ የሚኾን ታማኝ የሕዝብ ጋሻ ነው” በማለት የተቋማቱን አዲስ ቁመና ገልጸዋል።
ይህ ራስን የመቻል አቅም እና ሥር-ነቀል የተቋማት ሪፎርም ኢትዮጵያን በፈተናዎች መሐል የማይናወጥ ታሪካዊ የጥንካሬ ማማ ላይ ሰቅሏታል።
የጸጥታ ተቋማቱ ዛሬ የማይደፈር የሀገር ሉዓላዊነት ጋሻ ከመኾንም አልፈው ለቀጣናው የሰላም ምሶሶ መኾናቸው በተግባር እየተገለጠ ነው።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በቴክኖሎጂ ኢኮኖሚ።
Next articleባለፉት አምስት ዓመታት በሌማት ትሩፋት ምን መሠረታዊ ለውጥ መጣ?