
አትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘርፍ አዲስ ስትራቴጂ አንግባ የማይቻል የሚመስሉ ነገር ግን በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ በመኾን ፈጣን እና መሠረታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ። ይህም ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ ታጅባ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና ላይ መኾኗን የሚያሳይ የትውልድ ራዕይ ነው።
በተለይም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በባንክ እና በስታርት አፕ ዘርፎች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል። እጅግ ፈጣን የኾኑ የሞባይል ኢንተርኔት አውታረ መረቦች (4ጂ እና 5ጂ) በዋና ዋና ከተሞች እና በክልል ከተሞች የማዳረስ ሥራም ተከናውኗል። የዲጅታል ፋይናንስ እና የባንክ አገልግሎትን የማዘመን ሥራም ተሠርቷል።
ባሕላዊው የባንክ አሠራር ቀርቶ አብዛኞቹ ባንኮች ዘመናዊ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ከቤት ኾኖ ገንዘብ ማስተላለፍን፣ ቢል መክፈልን እና ሂሳብ ማስተዳደር አስችሏል። ለዚህም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ማሳያ ናቸው።
የመንግሥት ተቋማት ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡም ተደርጓል። ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በኦንላይን መስጠት በመጀመራቸው የቢሮክራሲ ኬላዎችን ለማስቀረት አስችሏል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ከመሥጠት ባለፈ ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት ያስቻለ አሠራርም ነው። በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት ተዘርግቶም ዜጎችን በዘመናዊ መንገድ የመለየት እና አገልግሎቶችን የማቀላጠፍ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
በርካታ ዜጎችም የኮደርስ ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። በስታርት አፕ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
በአጠቃላይ ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል። ይህም የተገልጋዩን ማኅበረሰብ ጊዜ፣ ጉልበት እና እንግልት በእጅጉ እየቀረፈ ይገኛል።
ለውጦች የዕለት ተዕለት ሕይወትን ቀላል ከማድረግ ባለፈ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ዲጂታል ዘመን እና ዓለም ለማሸጋገር ትልቅ መሠረት ጥለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አይሳከም የሚል ፍራቻ የነበረበት ነገር ግን ዕምርታዊ ለውጥ እያመጣ ያለ የዲጂታል ዘርፍ ነው ብለዋል። ማለም ማቀድ ብቻ ሳይኾን በተግባር መሳካት እንደሚቻል ያሳዬ መኾኑንም ነው የገለጹት።
የዲጂታል ኢኮኖሚያ ሽግግርም በብዙ ዘርፎች ስኬቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ነው የጠቆሙት።
በተለይም የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ስትራቴጂ የመረጃ ተደራሽነት እና ፍትሐዊነት እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ በዜጎች እና በተቋማት መካከል ጠንካራ መተማመንን መገንባት እንደኾነ አስረድተዋል።
በሂደቱም በመንግሥት እና በግል ተቋማት መካከል የተቀናጀ ግንኙነት የመፍጠር፣ አስተማማኝ የሳይበር ጥቃት የመከላከል ሥርዓት የመዘርጋት እና ቴክኖሎጂ-ሳቢ ትውልድ የመገንባት ሥራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።
የዲጂታል ሉዓላዊነት የዘመኑ ወሳኝ ጉዳይ በመኾኑ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ራሷን መቻል እና በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል። የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ከቀላል የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባሻገር በፈጠራ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን የሚያደርግ ታላቅ ሀገራዊ ምዕራፍ ነው።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
