ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን፣ የግዛት አንድነቷን እና ብሔራዊ ፍላጎቶቿን ለማስከበር ዝግጁ ናት።

21

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትቴር ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው ኢትዮጵያ በብዙኃኑ ዘንድ ብሉ ናይል በመባል የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ ምንጭ ናት ብሏል። የዓባይ ወንዝ የሚፈልቀው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ነው፤ ለናይል 85 በመቶ የሚኾነውን አስተዋጽኦ ታበረክታለች። ከዓባይ ወንዝ አጠቃቀም እና አሥተዳደር ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶች እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች ያገናዘቡ መኾን አለባቸው ብሏል መግለጫው።

በተመሳሳይ መልኩ ቀይ ባሕር ኢትዮጵያ በጂኦግራፊያዊ እና በታሪካዊ አጋጣሚዎች የተሳሰረችበት የባሕር አካል ነው። በጊዜ ሂደት በፖለቲካዊ ሁኔታዎች ለውጦች ቢደረጉም፣ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ቅርብ ቁርኝት እንደቀጠለ ነው፤ የቅርብ ድንበሯም ከባሕሩ ዳርቻ በ30 ማይል ርቀት ላይ ብቻ ይገኛል ነው ያለው።

በመኾኑም ስለ ቀጣናዊ የባሕር ጉዳዮች እና የደኅንነት መዋቅር የሚደረግ ማንኛውም ጠንካራ ውይይት የኢትዮጵያን ሕጋዊ ፍላጎቶች እና ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ዘላቂ ቁርኝት ያካተተ መኾን አለበት ነው ያሉት።

እነዚህን ጂኦግራፊያዊ እና ታሪካዊ እውነታዎች በፖለቲካዊ ንግግሮች እና በቀጣናው ላይ በሚደረጉ የማወክ ድርጊቶች መቀየር አይቻልም ብሏል።

የሚወሰዱ እርምጃዎች ወይም ትንኮሳዎች መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን አይለውጡም፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ሕጋዊ ፍላጎት፣ ሚና እና ኃላፊነት አያናጉም ነው ያለው።

ኢትዮጵያ ሰላማዊ ግንኙነትን እና ቀጣናዊ ትብብርን ማስቀደሟን ትቀጥላለች። ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን፣ የግዛት አንድነቷን እና ዋና ዋና ብሔራዊ ፍላጎቶቿን ለማስከበር ዝግጁ ናት።

ሁሉም የቀጣናው አካላት ከግጭት እና ከዜሮ ድምር አቀራረቦች ይልቅ ገንቢ በኾነ ውይይት፣ በጋራ አጋርነት እና በበጎ አጎራባችነት መርሆዎች በመመራት የጋራ ፈተናዎችን እንዲፈቱ ትጠይቃለች ብሏል መግለጫው።

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_25_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article💎 ከምድር ማሕጸን ወደ ሀገር ካዝና፤ የመንግሥት ስልታዊ አቅጣጫ! 💎
Next articleዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በቴክኖሎጂ ኢኮኖሚ።