
የኢትዮጵያ ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት እና ከዘመናት ማነቆዎች በመላቀቅ፤ በጠንካራ አመራር እና በሕዝብ ተሳትፎ መዋቅራዊ ለውጥ እያስመዘገበ ለመኾኑ “በእኛ ጊዜ ኢትዮጵያ ልመና ታቆማለች፤ የባከኑ ሀብቶቿ ይወጣሉ” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ንግግር ያሳያል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀገሪቱ ለዘመናት በምግብ እህል ራስን ባለመቻል እና በውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ በመኾን ያሳለፈችውን ፈተና ተናግረዋል። “ለበርካታ ዓመታት ከውጭ ስንዴ ለማስገባት በቢሊዮን ዶላር ስናወጣ እና የእርዳታ እህል ስንጠብቅ ኖረናል፤ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ሊኾን አይገባም” በማለት የነበረውን አሳሳቢ የውጭ ጥገኝነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የምግብ ዋስትና መጓደል ተግዳሮት አብራርተዋል።
መሪር እውነታውን ለመቀየር በተወሰደው ርምጃ የተገኘውን ድል የገለጹትም “ዝናብን ብቻ ጠብቆ የማምረት ልማዳችንን በበጋ መስኖ ልማት ሰብረነዋል፤ አሁን የራሳችንን ፍጆታ ሸፍነን ስንዴ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ጀምረናል” በማለት ነው።
ኢትዮጵያ በ2018 ዓ.ም ብቻ 318 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማምረት ሀገሪቱ ከስንዴ አስመጪነት ወደ ላኪነት ለመሸጋገሯ ማሳያ ነው።
ከስንዴ ልማቱ ስኬት ባሻገር በመላ ሀገሪቱ በስፋት እየተተገበረ ያለው የኩታ ገጠም የእርሻ ስልት በምርታማነት ላይ መዋቅራዊ ለውጥ አምጥቷል። አርሶ አደሮች አነስተኛ ማሳዎቻቸውን በማቀናጀት ትራክተሮችን እና ኮምባይነሮችን በመጠቀም ዘመናዊ የግብርና ሜካናይዜሽንን መተግበራቸው የምርት ብክነትን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
የሆርቲካልቸር ዘርፉም እንደ አቮካዶ ያሉ ምርቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ርዕይን መሬት እያስነካው ይገኛል። ይህም በኤክስፖርት ገቢ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አቅምን አሳድጓል።
ኢትዮጵያ በቡና ልማት እና ኤክስፖርት ባለፉት 17 ዓመታት ከተገኘው ገቢ በላይ በማስገኘት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ችላለች።
ለዚህም ስኬቱ ለግብርና ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት እንደኾነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዞው ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊያቆየው የቻለው ሌላው ግዙፉ ስኬት ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ያስገኘው ሥነ-ምህዳራዊ ድል ነው። ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የአፈር መሸርሸር እንዲቆም እና የከርሰ ምድር ውኃ መጠን እንዲጨምር መደረጉ ለበጋ መስኖ ስንዴ እና ለዘመናዊው ግብርና ጽኑ መሠረትን ጥሏል።
በግብርናው ዘርፍ የታየው የተቀናጀ ሀገራዊ መነቃቃት እና ስኬት ከሀገር አልፎ አህጉራዊ እውቅናን እያተረፈ ይገኛል።
የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት ፕሬዝዳንት አሊስ ሩዌዛ እንዳረጋገጡት ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና በእሴት ሰንሰለት ትስስር እያስመዘገበችው ያለው አስደናቂ ስኬት የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ለመላው አፍሪካ አርዓያ የሚኾን ነው።
የኢትዮጵያ ግብርና ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና ቴክኖሎጂ ሲታከልበት ሀገሪቱን ከጥገኝነት አውጥቶ ወደ ብልጽግና ማሸጋገር የሚችል መኾኑ ባለፉት ዓመታት ታይቷል።
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
Ameco #Agricultural_Transformation#Ethiopia_Prosperity
#ባሕር_ዳር #መስከረም_25_2019_ዓ_ም
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
