
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፍኖተ ካርታው ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉን አካትቶ ካሉበት ውሥብሥብ ችግሮች በማውጣት በዐይን የሚታዩ እና በእጅ የሚዳሰሱ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል።
ቀደምቷ ኢትዮጵያ ከወትሮው በባሕል፣ በተፈጥሮ ሃብት፣ በታሪክ እና በሃይማኖት እምቅ የቱሪዝም ሃብት የታደለች ናት። ነገር ግን እነዚህ ሃብቶቿ ያሉ እንጂ ያልተገለጡ ነበሩ። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ግን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ጸጋዎቿን በጥናት እና በልዩ ትኩረት በማልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በተግባር አጠናቅቃለች።
“ቅርሶችን እና ወሳኝ ፀጋዎችን ከቁስ ወደ ቁርስ የመለወጥ” አዲስ ብሔራዊ ስትራቴጂ በመቅረጽ ግዙፍ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት እንደ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ እና ግዙፉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መዲናዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል አድርገዋታል።
በክልል ደረጃ የተገነቡት እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ አላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ እና የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጅዎችን ያካተቱ የቱሪስት መስህቦች ኾነዋል።
ትኩረት ተነፍጓቸው የነበሩት የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፣ የታላቁ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት እና ሌሎች ሰፊ የጥገና እና የእድሳት ሥራ ተደርጎላቸው ከነበሩበት የመፍረስ አደጋ ወጥተው የቱሪዝም እንቅስቃሴያቸው እንደ አዲስ መነቃቃቱን ነዋሪዎች ጭምር የመሰከሩት ጉዳይ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየውም የቱሪዝም ዘርፍ ልማቱ ከተከናወነ ወዲህ በቱሪስት ፍሰት እና በገቢ የተገኘው ውጤት ካለፉት ዓመታት አኳያ ሲታይ እጅግ ከፍተኛ መኾኑ ተገልጿል።
ገቢው ከሚሊዮን ብር ወደ ቢሊዮን ዶላሮች፤ ፍሰቱ ከሺህዎች ወደ ሚሊዮኖች የተሸጋገረበት ለውጥ ተመዝግቧል። ይህ በዘርፉ የተከናወነው ልማት ለሀገሪቱ ኢክኖሚ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባለፈ በቀጥታ የተገነቡት መዳረሻዎች በሚገኙበት አካባቢ ለሚኖረው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ ኾኗል።
መንግሥት በቀጣይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ በርካታ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡ ይታወቃል።
ከእነዚህ ውስጥም “አንድ ወረዳ፤ አንድ መዳረሻ” በሚል የተቀረጸው መርሐ ግብር መልከ ብዙ የኾነችው ኢትዮጵያ በየስርቻው ያሏትን ቀሪ የቱሪዝም አቅሞች አውጥታ ተጠቃሚ እንድትኾን ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርላትም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
