በከፍተኛ ሙቀት የ450 ሺህ ሰዎች ህይወት ሊጠፋ ይችላል!

9
ባሕር ዳር: መስከረም 25/2019 ዓ.ም (አሚኮ) ኤልኒኖ፦ ውቅያኖስ ወለል ላይ በሚከሰት የውኃ ሙቀት መጨመር እና የተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት የሚመጣ ክስተት መኾኑን የዓለም ሜቲዮሮሎጅ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ይህ ክስተት በዓለም ዙሪያ የሙቀት ማዕበልን፣ የከፋ ድርቅን እና የጎርፍ አደጋዎችን በከፍተኛ ኹኔታ ያባብሳል። ​ሲ.ኤን.ኤን (CNN) የዓለም አቀፉን የሜቲዮሮሎጂ ድርጅት ሥጋት የሚያጠናክር አዲስ ዘገባ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
በመረጃው መሠረት አኹን ላይ የተከሰተው ኤል ኒኖ «ሱፐር ኤል ኒኖ» ወደሚባል እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ተሸጋግሯል። የቺካጎ ዩኒቨርሲቲን ጥናት መሠረት ያደረገው የመረጃ ምንጩ የኤልኒኖ ክስተት እና የሰው ሰራሽ አየር ንብረት ለውጥ በአንድ ላይ ተደምሮ ጉዳቱን አባብሶታል ብሏል።
ይህ የተቀናጀ አደጋ ከሰኔ 2026 እስከ የካቲት 2027 ባሉት ወራት ውስጥ 450 ሺህ ሰዎችን በከፍተኛ ሙቀት ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
​
✍️ተጨማሪ የጥናቱ ትንበያዎች፦ #የሙቀት መጨመር፦ ኤልኒኖ በመጭዎቹ ወራት የዓለምን የሙቀት መጠን ከተለመደው በ1 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ያደርገዋል። ይህም ከተለመዱት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የከፋ የሙቀት ቀናት ብዛትን በ44 በመቶ ይጨምራል።
#ከፍተኛ ኹኔታ የሚጎዱ ሀገራት፦ ጉዳቱ በዋናነት በደቡብ ክፍለ ዓለም (Global South) ሀገራት ላይ የሚበረታ ይኾናል። ናይጄሪያ የመጀመሪያዋ ከፍተኛ ጉዳት የምታስተናግድ ሀገር ትኾናለች ተብሎ ይጠበቃል። ኢንዶኔዥያ፣ ሱዳን፣ ሕንድ፣ ብራዚል እና አሜሪካ በከፍተኛ
ሥጋት ውስጥ እንደሚገኙም ተጠቅሷል።
✍️መወሰድ ያለባቸው መፍትሔዎች፦
#ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን በስፋት መዘርጋት፣
#የጤና ድንገተኛ ጊዜ እቅዶችን ማዘጋጀት፣
#የማቀዝቀዣ እና የውኃ አቅርቦት ማዕከላትን ማፋፋት፣
#የሕክምና አገልግሎቶችን ለአደጋው ተጋላጭ ለኾኑ ወገኖች ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ ጥናቱ መክሯል።
✍️ጥናቱ በባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ተገምግሞ ከማለቁ በፊት ይፋ የተደረገበት ምክንያት መንግሥታት እና ፖሊሲ አውጭዎች አደጋው ከመድረሱ በፊት የሰዎችን ሕይወት ለማዳን የሚያስችሉ አስቸኳይ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ለማስቻል ነውም ተብሏል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአቶ ዱባለ አብራሬ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኾነው ተሾሙ።
Next articleከደካማ እንቅስቃሴዎች ወደ ቢሊዮን ዶላሮች የተሸጋገረው የኢትዮጵያ የቱሪዝም