
የመደመር መንግሥት ብቁ እና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታውቀዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ የ2019 በጀት ዓመት የተማሪዎች ምገባን አስጀምረዋል።
በዘንድሮው ዓመት በክልሉ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የምገባ መርሐ ግብር ይካሔዳል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።
ተማሪዎች በጥሞና እና በተሻለ ምቾት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማስቻል መጠነ ማቋረጥን መቀነስ እንደሚገባም ተናግረዋል። እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ አበረታች ውጤት አሳይቷል ነው ያሉት።
በተለይም በመደበኛ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ላይ የነበረውን የትምህርት ማቋረጥ ለማስቀረት ወሳኝ ድርሻ አበርክቷል ብለዋል።
የምገባ መርሐ ግብሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ባለድርሻ አካላት መደገፍ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። በተለይም ከግብርና ሥራዎች ጋር በማስተሳሰር በሌማት ትሩፋት ውጤቶች ቢደገፍ ወጪን ቀንሶ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ያግዛል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ ከሚሠራው እና ከሚያመርተው ለተማሪዎች ምገባ መደገፍ እንዲለማመድ መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል።
ሀገራችን ያላት የሕዝብ ጸጋ በክህሎት፣ በዕውቀት እና የተሻለ አቅም የታጠቀ እንዲኾን ለማስቻል የትምህርት ዘርፍ ሥራ ስኬት ወሳኝ እንደኾነ ነው የገለጹት። ከዚህ አኳያም የትምህርት ተሳትፎ እና ጥራትን ለማረጋገጥም ትኩረት በመስጠት እየተሠራ መኾኑን አመልክተዋል።
እነዚህ ሥራዎች ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይኾን የሁሉንም አካል ድጋፍ የሚፈልጉ እንደኾነ ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
