የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

12
የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የፖሊሲ አቅማቸውን በመገንባት እና ልማት ተኮር አሥተዳደርን በማስፈን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን መሪዎች እንዲኾኑ ለማስቻል ያለመ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።
ጉባኤውን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ነብዩ ስዑል ከጥቅምት 26/2019 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም ለተከታታይ ሦሥት ቀናት በዓድዋ ድል መታሰቢያ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ 20 የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ብለዋል።
ጉባኤው በዋናነት የፖለቲካ ፓርቲዎች በአፍሪካ ልማት ላይ ያላቸው ሚና የሚመከርበት ይኾናል ነው ያሉት። “ዕድገትን መምራት የፓለቲካ ፓርቲዎች እንደ ኢኮኖሚ መፃኢ መሀንዲሶች” በሚል መሪ መልዕክት ጉባኤው እንደሚካሄድም ገልጸዋል።
በጉባኤው የአህጉሪቱ የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ አሳታፊ እና ዘላቂ ዕድገት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት እና የፋይናንስ አሥተዳደር ተጠያቂነት ላይ ትኩረት አድርገው ይወያያሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንድታካሄድ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷ፣ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ሀገር መኾኗ እና እንደሀገር በተለያዩ ዘርፎች ያሳካቻቸው እመርታዎች ምክንያት እንደኾኗት ጠቅሰዋል።
ከ54ቱም የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች በሚገኙበት በዚህ ጉባኤ ላይ የሴቶች፣ የወጣቶች እና የመሪዎች መድረኮች ይካሄዳሉ ተብሏል።
ፓርቲዎች መክረው በጋራ የተግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ የአቋም መግለጫ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። የከተማዋ ሕዝብም የጉባኤውን ሂደት በመከታተል በተለመደው እንግዳ ተቀባይነቱ እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል።
✍️ ዘጋቢ:-ቤቴልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአሸባሪዎች መቅሰፍት-የቀጣናው የሰላም ዋስትና-የሀገር መከላከያ ሠራዊት!
Next article“ብቁ እና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየሠራን ነው” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ