የአሸባሪዎች መቅሰፍት-የቀጣናው የሰላም ዋስትና-የሀገር መከላከያ ሠራዊት!

12
በምሥራቅ አፍሪካ በየወቅቱ የሚከሰቱ የፖለቲካ ግጭቶች በቀጣናው አማጺያን ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርገዋል። ለአብነት የአልሸባብ አማጽያን ቡድን እና ሌሎች አማጽያኖች የቀጣናውን ሰላም ለማናጋት ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል።
የምሥራቅ አፍሪካን መረጋጋት፣ ሰላም እና ልማት የማይፈልጉ ሀገራት አማጽያን ቡድኑን ሲደግፉ ይስተዋላል። ከቀጣናው ውጭ ያሉ ሀገራትን ተልዕኮ በመፈጸም፣ የሀገርን ሉዓላዊነት በመዳፈር፣ የሌሎች ሀገራትን ድንበር በመጣስ ጥቃቶችን በመፈጸም ብጥብጥ እና ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ አማጺ ቡድን ሀገሪቱን ለዓመታት ወደ ኋላ እንድትጓዝ አድርጓታል። ይህንን ቡድን ለማጥፋት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኀይል ለዓመታት የቀጣናውን ሰላም ለማጽናት ከሌሎች ሰላም አስከባሪዎች ጋር በመኾን መስዋዕትነት ከፍሏል።
ይህም ኢትዮጵያ በታሪክ ለቀጣናው ሰላም ስታደርገው የነበረውን ጥበቃ አጠናክራ መቀጠሏን ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ ከሉዓላዊነቷ አልፎ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ዋስትና የሚኾን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመገንባት ላይም ትገኛለች።
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አቅም ከፍ ማለት ደግሞ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ከፍተኛ ፋይዳ አለው። ኢትዮጵያ ድሮኖችን፣ ተወንጫፊ የጦር አውሮፕላኖችን እና ሌሎች ዘመኑን የሚመጥኑ የጦር ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ የቀጣናውን ጠንካራ ሠራዊት ገንብታለች።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የገዛቻቸው የጦር ጄቶች ከራሷ አልፎ የቀጣናውን ሰላም ይበልጥ ለማረጋገጥ ያላትን ፍላጎት ያንጸባርቃል። የጦር ቴክኖሎጂዎችን በራስ አቅም ማምረት፣ በመጠገን እና ብቁ የሰው ኀይልን በማፍራት ስኬት እያስመዘገበ የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለቀጣናው ሀገራት የልምድ ማዕከል በመኾን ላይ ይገኛል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት አቅም ከፍ ማለት በቀጣናው ላይ የሚፈጸምን የአሸባሪዎች ጥቃት ለመከላከል፣ የአማጽያንን ተልዕኮ ለማክሸፍ፣ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ከሩሲያ የገዛቻቸውን የጦር ጄቶች በተረከቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በቂ ዝግጅት ያላቸው ሀገራት በቀላሉ አይደፈሩም ብለዋል። መዘጋጀት ውጊያን ያስቀራል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዝግጅት በአፍሪካ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል። ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አለኝታ እና መከታ ለመኾን ኢትዮጵያ እየሠራች መኾኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለማስቀረት ዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂ የታጠቀ ሰላም እና መረጋጋትን የሚፈጥር ጠንካራ ሠራዊት መገንባቷን ገልጸዋል። ሠራዊቱ ለቀጣናው ዋስትና ኾኖ ይቀጥላል ነው ያሉት።
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአቶ አሕመድ አሊ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኾነው ተሾሙ።