
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ በክልሉ የተቀናጀ የውኃ ሀብት አሥተዳደር እና አጠቃቀም በተመለከተ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
የዓባይ ቤዚን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዮሐንስ መላክ በዚህ ወቅት እንዳሉት መሬትን እና ውኃን በአግባቡ በማሥተዳደር ለቀጣዩ ትውልድ በቀጣይነት ለማስረከብ በቅንጅት መሥራት ይገባል።
ፕሮጄክቶች እና ፈጻሚ ተቋማት ከተናጠል አሠራር ወጥተው የልማት ሥራዎችን እና የውኃ ሀብት አሥተዳደርን በቅንጅት በመሥራት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የዓባይ ቤዚን ከሀገሪቱ ካሉት 12 ቤዚኖች እስከ 50 በመቶ የሚደርሰውን የውኃ መጠን እንደሚይዝም ገልጸዋል።
ከፍተኛ መሥኖ የማልማት አቅም እንዳለውም ተናግረዋል። ይህንን የውኃ ሀብት በሚገባ መጠቀም እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
በወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት የመርሐግብር እና ጥናት ባለሙያ ሙሉነህ ቢምረው እንደተናገሩት ከዚህ በፊት ተቋማት ተቀናጅተው ባለመሥራታቸው የውኃ አጠቃቀም ውጤታማ እንዳይኾን አድርጎታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የተቀናጀ ዘላቂ የውኃ አጠቃቀም ማዕቀፍ ተቋቁሞ በትብብር በመሠራቱ ለውጦች እየታዩ እንደሚገኙ አንስተዋል። አንዳንድ ቦታዎች ላይም የሙከራ ጥናቶች እየተሠሩ መኾኑን አመላክተዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት ቢሮው በተለይም ከተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በተተገበረው ቅንጅታዊ የተፋሰስ ልማት በተለይም በመኖ አቅርቦት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ውጤት እየመጣ ነው ብለዋል። ከኅብረት ሥራ ኮሚሽን ጋር በመተባበርም የተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዓመቱን ሙሉ የተፋሰስ ሥራ እንዲያከናውኑ እየተደረገ መኾኑን አብራርተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
