
ብቁ እና ነገ ሀገርን የሚረከቡ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ደረጃቸውን የጠበቁ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን መገንባት ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው።
በአማራ ክልልም በፌዴራል መንግሥት በትምህርት ሚኒስቴር ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተገነቡ የሚገኙ አራት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። እነዚህ ትምህርት ቤቶች በአንድ ዓመት የሥራ ውል ተይዞላቸው በ2018 ዓ.ም ነበር ግንባታቸው የተጀመረው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ እየተገነቡ የሚገኙ ሞዴል ትምህርት ቤቶች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በዚህም የሞዴል ትምህርት ቤቶች የግንባታ አፈጻጸም ፦
ሞዴል ትምህርት ቤቶቹ በወቅቱ እንዲጠናቀቁ የቅርብ ክትትል ሲደረግ ቢቆይም በወቅታዊ ሁኔታው እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተያዘላቸው ጊዜ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። የቀሩ ያልተሟሉ ቁሳቁሶችን በማሟላት ግንባታቸውን አጠናቅቆ ሥራ እንዲጀምሩ ጥረት እየተደረገ ይገናኛል ነው ያሉት።
ሞዴል ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎች ሙሉ ቀን እንዲማሩ የሚያስችሉ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች፣ ብቁ መምህራን እና አስፈላጊ ዘመናዊ የትምህርት ግብዓቶች የሚሟሉላቸው ናቸው ብለዋል።
በተለይም በአካባቢው የሚገኙ የተሻሉ ተማሪዎች እና ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የመግባት ዕድል ያላገኙ ብቁ ተማሪዎችን በመቀበል፣ በቂ ዕውቀት እንዲጨብጡ እና ሀገር የሚገነቡ ውጤታማ ዜጎች ለማፍራት የሚያገለግሉ መኾናቸውን አንስተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ የሥጋት ደሴ እየተገነባ የሚገኘው የፍኖተ ሰላም ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው በመጠናቀቅ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ የዕውቀት ማዕከል ኾኖ የሚያገለግል እንደኾነም ጠቅሰዋል። ይህ ሞዴል ትምህርት ቤት ሲጠናቀቅ፣ በክፍል ውስጥ የሚስተዋለውን የመጨናነቅ ችግር በመፍታት የተማሪ ክፍል ጥምርታን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።
በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና የሚጫወት እና የተሞክሮ ማዕከል የሚኾን ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ የፈጠራ ማዕከል ኾኖ ተወዳዳሪ እና ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት የሚያስችል ነው፤ ይህም ተመሳሳይ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን በስፋት ለመገንባት በር የሚከፍት ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ቀሪ አስፈላጊ የመሠረተ ልማት እና የቁሳቁስ አቅርቦቶችን በማሟላት ትምህርት ለማስጀመር በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ሞዴል ትምህርት ቤቶች የተሻለ የመማር ማስተማር ሥርዓት የሚከናወንባቸው ናቸው። ይህም ብቁ እና ነገ ሀገርን የሚያሻግሩ ዜጎችን በማፍራት ትልቅ የዕውቀት ማዕከል እንደኾኑም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
