ከተስፋ ወደ ምርት፤ የባሕር ዳር ከተማ የኢንቨስትመንት ጉዞ

14

🇪🇹
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳርን ለመፍጠር ትኩረት አድርጓል። አዳዲስ ፈቃዶችን በመስጠት፣ መሬት በማዘጋጀት፣ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት እና የማምረት እና የውጭ ምንዛሬ አቅም ማሳደግን ቀዳሚዎቹ ተግባራት አድርጓል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በ2018 በጀት ዓመት 383 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን አስታውሰዋል። ለ301 አምራች ኢንዱስትሪዎች ከሦስተኛ ወገን ነጻ የኾነ 110 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የታቀዱትን 23 አምራች የኢንዱስትሪ ፕሮጄክቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት። የ85 ኢንዱስትሪዎች የመሠረተ ልማት ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ59 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም አመላክተዋል። ረጅም ጊዜ ቦታ አጥረው ወደ ሥራ ያልገቡ 53 ፕሮጄክቶች ተለይተው ለ32ቱ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ብለዋል።
21 ባለሀብቶች ደግሞ የወሰዱትን 13 ነጥብ 93 ሄክታር መሬት እንዲነጠቁ መደረጉን አረጋግጠዋል።
በሀገር ውስጥ ገበያ በ43 ኢንዱስትሪዎች መካከል የምርት ትስስር መፈጠሩንም ተናግረዋል።
በውጭ ንግድ ዘርፍም በዘጠኝ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና በስምንት የምርት አይነቶች 17 ሺህ 192 ነጥብ 6 ቶን ምርት በመላክ 22 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው የገለጹት።
አሁንም ኢንቨስትመንትን የከተማዋ መለያ አድርጎ ለማስቀጠል ጠንካራ የክትትል እና ድጋፍ ሥርዓት መዘርጋት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን ማቀላጠፍ፣ የውጭ ምንዛሬ አቅም የምርት ጥራትን ማሳደግ እና ሰፊ የምርት ትስስር መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበአማራ ክልል እየተገነቡ የሚገኙ ሞዴል ትምህርት ቤቶች የት ደረሱ ?
Next articleአቅምን ያገናዘበ አገልግሎት ለከተማዋ ሕዝብ እየሰጡ ያሉት የከተማዋ አውቶብሶች