አቅምን ያገናዘበ አገልግሎት ለከተማዋ ሕዝብ እየሰጡ ያሉት የከተማዋ አውቶብሶች

17

 

የአማራ ክልል መንግሥት ከተሞችን የማዘመን እና አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረግ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል። በተለይም በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የሚኖረው ማኅበረሰብ ከእንቅስቃሴ እና ከትራንስፖርት እንግልት እንዲገላገል የተደረገው የከተማ አውቶብስ ስምሪት ለአብነት የሚጠቀስ ሰው ተኮር ልማት ኾኗል።

ባለፉት ጊዜያት በባሕር ዳር፣ በደሴ፣ በጎንደር እና በሌሎችም የክልሉ ከተሞች የሕዝብ ትራንስፖርት እጥረት እና የትራንስፖርት ዋጋ ንረት በዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት እና በአጋር ድርጅቶች በተለይም ወደ ባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ወልዲያ እና ጎንደር ከተሞች የገቡት የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ አውቶብሶች የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በእጅጉ አቅልለዋል።

በክልሉ ዋና ከተማ ባሕርዳር የተጀመረው የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ተማሪዎችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን እና የንግዱን ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማጓጓዝ ላይ ይገኛል። በደሴ እና በጎንደር ከተሞች የከተማ አውቶብሶች ስምሪት በተለይም የኑሮ ውድነቱን ተቋቁመው ለሚንቀሳቀሱ ዜጎች ትልቅ የኢኮኖሚ እፎይታ ሰጥቷል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በቅርቡ በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመላከቱት ከተሞችን በማዘመን እና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። በከተሞች መልካም አሥተዳደርን ማረጋገጥ እና መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ዋነኛ ትኩረት መኾኑንም ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሰባት ዋና ዋና የክልሉ ከተሞች እና በአነስተኛ ከተሞች ጭምር እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት እና የመንገድ ማሻሻያ ሥራ ለከተማ ትራንስፖርት ምቹነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የአገልግሎት አሰጣጥ ቢሮክራሲን ለማስቀረት እና ዜጎችን ከእንግልት ለመታደግ ደግሞ የተጀመሩ የተቀናጁ አሠራሮችም ከትራንስፖርቱ ዘርፍ ጋር ተሳስረው እየተተገበሩ እንደኾነ አንስተዋል።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንችአምላክ ገብረማርያም ደግሞ በክልሉ የተጀመረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ የመንግሥት አሠራርን ፈጣን እና ቀልጣፋ በማድረግ የባለጉዳዮችን እንግልት እና ወጪ እየቀነሰ እንደኾነ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። እንዲህ ዓይነት ልማቶች የዜጎችን ሰብአዊ ክብር እና ማኅበራዊ ትስስር የሚጠብቁ በመኾናቸው ማኅበረሰቡ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየደገፋቸው እንደሚገኝም አመላክተዋል።

በአማራ ክልል የተጀመሩትን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አውቶብሶች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የጸጥታ ሁኔታዎችን አስተማማኝ በማድረግ የዘመናዊ አውቶብሶችን ስምሪት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ደግሞ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት ለአሚኮ ሀሳባቸውን መስጠታቸው የሚታወስ ነው። የከተማ የሕዝብ ትራንስፓርት አገልግሎት ስምሪት ማስፋፋትም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነጥቦች መኾናቸውን ጠቁመዋል።

በጥቅሉ ልማት ሰውን ማዕከል ሲያደርግ እና እንደ ከተማ አውቶብስ ያሉ ወሳኝ ፍላጎቶችን ሲያሟላ የሕዝቡ እርካታ እና ተጠቃሚነት በተግባር እንደሚረጋገጥ የአማራ ክልል ከተሞች ጅምር ተሞክሮ ያሳያል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#አገልግሎትአሰጣጥ#አማራክልል#አሚኮ
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_25_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከተስፋ ወደ ምርት፤ የባሕር ዳር ከተማ የኢንቨስትመንት ጉዞ
Next articleኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ወታደራዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ።