
የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ከውጭ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር የሚያደርጉትን ተከታታይ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ውይይት በመቀጠል በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረውን ታሪካዊ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ፣ በወታደራዊ እና ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል።
የመከላካያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ፈረንሳይ አሁናዊ እና ስትራቴጂያዊ ወታደራዊ አቅምን ለማሳደግ እያደረገች ላለችው የዕውቀት ሽግግር እና የሰላም ማስከበር ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር እያደረገች ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ፍትሐዊ እና ሕጋዊ ጥቅሟን ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት ፈረንሳይ ከጎኗ እንድትቆምም ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን የመልሶ ማቋቋም እና የሠራዊት ማዋሃድ (DDR) ሂደት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፈረንሳይ ለሂደቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት እና ሁለገብ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለአሚኮ በላከው መረጃ እንዳመላከተው በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች፣ በወታደራዊ ሥልጠናና አቅም ግንባታ ዘርፎች የሚከናወኑ የጋራ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_25_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
