ጠንካራ ተቋማት ሀገርን ተሸክመው የሚቆሙ መሠረቶች ናቸው።

11
🏛️
ሀገርን በዘላቂነት የሚያስቀጥለው እና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያሻግረው ጊዜያዊ ሞገስ ከተቸራቸው ጠንካራ ግለሰቦች በላይ የላቀ ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋም ሲገነባ ነው።
የፍትሕ፣ የጸጥታ፣ የዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ኾነው የሕዝብ አመኔታን ካላተረፉ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ አይቻልም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተቋም ግንባታ የመንግሥት ምሰሶ መኾኑን “ከጠንካራ ግለሰቦች ይልቅ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉናል፤ ግለሰቦች ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ተቋማት ግን ሀገርን ተሸክመው ይቆያሉ” ማለታቸው ይታወሳል። ይህም በግለሰብ ትከሻ ላይ ከተንጠለጠለ ሥርዓት ወጥቶ በሕግ እና በአሠራር ወደሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት መሸጋገር እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው።
ምሁራን እንደሚያስገነዝቡት ጠንካራ ተቋማት ለሀገር ህልውና ወሳኝ ሚና አላቸው። ፕሮፌሰር ዳሮን አሴሞግሉ እና ጀምስ ሮቢንሰን በ”ሀገራት ለምን ይወድቃሉ?” መጽሐፋቸው እንዳብራሩት የሀገራትን መበልጸግም ኾነ መክሰም የሚወስነው የተቋማቶቻቸው ተፈጥሮ ነው ሲሉ አትተዋል።
አካታች የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተቋማት ያላቸው ሀገራት የዜጎችን የፈጠራ አቅም በማጎልበት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ብልጽግናን አረጋግጠዋል።
የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ፍራንሲስ ፉኩያማ እውነተኛ ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት ሊሰፍን የሚችለው ሕግን ማስከበር የሚችል ብቃት ያለው እና ከሙስና የጸዳ ጠንካራ የመንግሥት ተቋም ሲገነባ ብቻ መኾኑን ይሞግታሉ።
ተቋማት ሲጠነክሩ እና ለሕዝብ ሲወግኑ የዜጎች አመኔታ ይጨምራል፤ ማኅበራዊ ፍትሕ ይሰፍናል፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ይስባል፤ በምርጫ የሚመጣ የፖለቲካ ሽግግር ሀገርን የማያናውጥበት ጽኑ ምሰሶ ይፈጠራል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የመንግሥት ምስረታ እየተካሄደ ነው። በቀጣዮቹ ዓመታት የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት ማዕከል መኾን ያለበት የሰዎችን ግላዊ አቅም ከመገንባት ባለፈ ትውልድ ተሻጋሪ እና በነፋስ የማይናወጥ ጠንካራ ሀገራዊ የተቋም አቅም መፍጠር ነው።
በአማራ ክልል በተካሄደው የመንግሥት ምስረታ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለጠንካራ ተቋማት ግንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት እንዲሁም ተቋማት የዜጎችን ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንዲችሉ ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ፣ በሕግ መሰረት ሕዝብን የሚያገለግሉ እና ለሕግ የቆሙ ሙያዊ ተቋማት ኾነው እንዲገነቡ ይሠራል ብለዋል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 🇪🇹
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያውያን የሥነ መንግሥት እሳቤ እስከምን ድረስ ነው?
Next articleአቶ አየን ብርሃን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ኾነው ተሾሙ።