አካታች የፖለቲካ እና የትብብር ባሕል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ

9
🇪🇹
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የታዩ የፖለቲካ እድገቶች እና የተካሄዱ የካቢኒ ሽግግሮች በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሂደት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች መኾናቸውን የዘርፉ ምሁራን እና የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።
በምርጫ ያሸነፈው ገዥ ፓርቲ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ሥልጣን በመካፈል ያሳየው አካታችነት፤ በፉክክር እና በትብብር መካከል የነበረውን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይገልጻሉ። ይህ ተሞክሮ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ባሕል እንዲጎለብት፣ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር እና ለአንዲት ሀገር ህልውና በጋራ የመሥራት ልምድ እንዲዳብር ማድረጉንም ያመላክታሉ።
የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ተመራማሪው ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ለአፍሪካ የሰላም እና ደኅንነት ጥናቶች ተቋም (IPSS) የሰጡት ማብራሪያ ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራል። የእርሳቸው ገለጻ በሽግግር እና በለውጥ ወቅት ላይ ያሉ ሀገራት ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚችሉት ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ የፖለቲካ ምህዳር ሲፈጥሩ እንደኾነ ያስረዳል።
ሥልጣንን ማካፈል እና ተፎካካሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት የተቃውሞ ፖለቲካን ወደ ገንቢ የፖለቲካ ማዕቀፍ የሚቀይር፣ የሕዝብን መተማመን የሚጨምር እና የሀገር ግንባታን የሚያፋጥን ዋና መሳሪያ እንደኾነም አብራርተዋል።
ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍል ትንተናዎች እና ሀገራዊ የውይይት መድረኮች ላይ እንደገለጹት ሀገራዊ መግባባትን እና አካታችነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ባሕል መገንባት ለአንድነት እና ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል። ተፎካካሪ ኃይሎች በጋራ ጉዳዮች ላይ በካቢኒ እና በተለያዩ ሀገራዊ መድረኮች አብረው እንዲሠሩ መደረጉ የፖለቲካ ፉክክር በጠላትነት ሳይኾን በትብብር እና በአስተሳሰብ የበላይነት ላይ እንዲመሰረት አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።
የፖለቲካ እና የአመራርነት ተመራማሪው ዶክተር ምህረት ደበበ ደግሞ አካታች የፖለቲካ እና የትብብር ባሕል ለቀጣይዋ ኢትዮጵያ ያለውን አስተዋጽኦ ሀገራዊ የምሁራን የፖለቲካ መድረኮች ላይ ሲገልጹ የተጀመረው በፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር እና በትብብር መካከል ያለው ሚዛን ለአዲሷ ኢትዮጵያ ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል አብራርተዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እና ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማትን ለመገንባት የተፎካካሪዎች እና የልዩ ልዩ አስተሳሰቦች መኖራቸው የረጅም ጊዜ ሀገራዊ መረጋጋትን ያረጋግጣልም ብለዋል።
እንደ ምሁራኑ ማብራሪያ አካታች የፖለቲካ እና የትብብር ባሕል ለቀጣይዋ ኢትዮጵያ ከሚኖረው አወንታዊ አስተዋጽኦ መካከል መተማመንን መገንባት አንዱ እንደኾነም አንስተዋል። በሥልጣን ላይ ያለው አካል እና ተፎካካሪዎች በጋራ መሥራታቸው በፖለቲካ ኃይሎች መካከል የቆየውን ክፍተት ያጠባል ነው ያሉት።
ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልንም ያጠናክራል። ሃሳብን በዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የማንጸባረቅ ባሕልን ያጎለብታል። የጋራ ልማት እና እድገትን ይፈጥራል። የሀገሪቱን የተለያዩ ዕውቀቶች እና አቅሞች አጣጥሞ በመጠቀም ለሀገር እድገት በአንድነት ለመቆምም ያስችላል።
አካታች እና አሳታፊ የፖለቲካ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ለነገዋ ኢትዮጵያ አስተማማኝ መሰረት የሚጥል በመኾኑ ይህ በጎ ልምድ በቋሚነት እንዲጎለብት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት አስፈላጊ ይኾናል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ 🇪🇹
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያውያን የሥነ መንግሥት እሳቤ እስከምን ድረስ ነው?
Next articleየኢትዮጵያ ታላቅ የድል ብስራት ቀን!