
ሕዝቦቿ በየዘመናት የተጋረጡባቸውን የውጭ ወረራዎች በአንድነት እና በጽናት በመመከት ያስመዘገቧቸው ድሎች የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ችቦ በመኾንም አህጉራዊ ኩራትን አጎናጽፈዋል።
ይህንን በወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ፣ የአፍሪካዊ የጀግንነት ፍኖት፣ ዘመን የማይሽረው ጥንካሬ፣ አህጉራዊ ተፅዕኖ እና አቅም ጥቂት የጎረቤት ሀገራት ይክዱታል። በተለይም ግብጽ እና ኤርትራ የኢትዮጵያን አንድነት፣ መረጋጋት እና ሁለንተናዊ ዕድገት በስጋት ይመለከቱታል።
የግብጽ ፍላጎት በዋናነት ከዓባይ ውኃ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው። ለዚህም የምትከተለው የጂኦ-ፖለቲካ እስትራቴጂ ኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት፣ የተረጋጋ ሰላም እና የዳበረ ኢኮኖሚ እንዳይኖራት ማድረግን ዓላማ ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ ወደ ልማት ፊቷን ባዞረች ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሃብቷን ለመጠቀም ስትነሳ፣ ግብጽ የሀገሪቱን የውስጥ ክፍተቶች በመጠቀም አማጺ ቡድኖችን በመደገፍ በእጅ አዙር በመጉዳት ትታወቃለች። ይህ ሴራዋ ከጥንት ጀምሮ የምትከተለው ስትራቴጂ ስለመኾኑ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ (ከ1847 እስከ 1983) በሚለው መጽሐፋቸው በስፋት አብራርተውታል።
ዛሬም ድረስ ከቀጣናው ሀገራት እና ከአማጺ ቡድኖች ድጋፍ ባለፈ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ እስከ ማሳሳት የደረሰ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ማማተሯን ቀጥላበታለች።
ኤርትራም ኢትዮጵያ በቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪ እና የበለጸገች ሀገር ኾና እንዳትወጣ ትፈልጋለች። ለዚህም የኢትዮጵያ የውስጥ አንድነት እንዳይጠናከር፣ በቋሚ የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ የሚያደርጉ ሴራዎችን ስትደግስ እና ስታስፈጽም ኖራለች።
በቀጥታ ድንበር ተሻጋሪ ጣልቃ ገብነቶች፣ የታጠቁ ቡድኖችን በመደገፍ፣ እንዲኹም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች እጇን በማስገባት ኢትዮጵያን ለማዳከም ብዙ ጥራለች።
ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ በየጊዜው የሚያወጣቸው የአፍሪካ ቀንድ የደኅንነት ሪፖርቶችም ይህንን የኤርትራን ሴራ እና በኢትዮጵያ የውስጥ ጣልቃ ገብነት ድርጊቶችን በጥልቀት ይተነትናሉ።
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ታሪካዊ እና አሁናዊ የጂኦ-ፖለቲካ ጫናዎች በጥበብ በማለፍ ቀጣናዊ መሪነቷን እና አህጉራዊ አርዓያነቷን አስጠብቃ ለመጓዝ የሚያስችላትን አቅም ገንብታለች።
የኢትዮጵያ አንድነት እና አይበገሬነት ከራሷ አልፎ ለመላው አፍሪካውያን የነፃነት እና ኩራት ምልክት እንደነበር ሁሉ ዛሬም የውስጥ እና የውጭ ሴራዎችን ማክሸፍ የሚያስችላት አቋም ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ ዝግጅት ከራሷ አልፎ በድፍን አፍሪካ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ላሉ ሀገራት ደግሞ አለኝታ፣ መከታ እና ጋሻ መኾንን ዓላማ ያደረገ ስለመኾኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አረጋግጠዋል።
በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
